ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ ዩክሬን የሃይል አቅርቦቷን ለመመለስ እየታገለች ነው
ሩሲያ ከፍተኛ የሚሳኤል ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ ዩክሬን እስከ 50 በመቶ የሚሆነው የሃገሪቱ የኤሌክትሪክ ፍላጎት አለመሟላቱን ተናግራለች።
ዩክሬኔርጎ የተባለው የኃይል አገልግሎት ተቋም ቅድሚያ የሚሰጠው መሠረተ ልማቱን ማስተካከል ቢሆንም ጥገናው ብዙ ጊዜ ወስዷል ብሏል።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ "በጣም አስቸጋሪ" የኃይል እና የውሃ አቅርቦት ዋና ከተማዋ ኪዬቭን ጨምሮ በ 15 ክልሎች መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
በመላው ዩክሬን በበረዶ እና ከዜሮ በታች የሆነ አጥንት የሚሰብር ቅዝቃዜ የተቀላቀለበት ክረምት እየገባ ነው።
በመላ አገሪቱ ያሉ ሰዎች በቅዝቃዜ ምክንያት ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ሐሙስ ዕለት 70 በመቶ ያህሉ የኪዬቭ ነዋሪዎች የኃይል አቅርቦታቸው ተቋርጧል።
የኪዬቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ ለቢቢሲ ዩክሬን እንደተናገሩት ከተማዋ ያለ መብራት፣ ሙቀት እና ውሃ የምትቆይበት ጉዳይ "የከፋ ሁኔታ" ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።
በኋላ ላይ የዩክሬን ባለስልጣናት የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት በሁሉም ክልሎች ቀስ በቀስ እየተመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“በመጨረሻም [ባለሥልጣናቱ] ኤሌክትሪክ አስጀምረውልናል” ብለዋል።
ቶኒያ የተባለች ሌላኛ የኪዬቭ ነዋሪ ለ48 ሰዓታት መብራት እንዳልነበራት ሃሙስ አመሻሽ ላይ ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ሃይል ባይኖረውም አሁን ውሃ አለኝ። አሁንም ግን መብራት የለም" ብላለች።
"ለ120 ቀናት የሚቆየው ክረምት"
የዩክሬን ባለስልጣናት በመላ ሀገሪቱ ከ4 ሺህ በላይ ጊዜያዊ ማሞቂያ ድንኳን አቋቁመዋል። ይህም ነዋሪዎች ስልኮቻቸዉን ቻርጅ የሚያደርጉበት እና ሻይ ወይም ቡና የሚያገኙበት ነው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ሐሙስ ዕለት ባደረጉት የቪዲዮ ንግግር የሩሲያ ወታደሮች “እንዴት እንደሚዋጉ አያውቁም” ብለዋል።
“አሁንም ማድረግ የሚችሉት ብቸኛው ነገር ሽብር ነው። የኃይል ሽብር፣ የመድፍ ሽብር፣ ወይም የሚሳኤል ሽብር። ሩሲያ አሁን ባሉት መሪዎቿ ወደዚህ ደረጃ ወርዳለች” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሪና ቬሬሽቹክ ለቢቢሲ ወርልድ ቱናይት ፕሮግራም "አሸባሪዋ ሩሲያ በእኛ ላይ የኃይል ጦርነት ጀምራለች። ዓላማው ትልቅ ሰብአዊ ቀውስ ለመፍጠር ነው። ለኛ ትልቁ ፈተና በጣም ተጋላጭ የሆኑትን አረጋውያንን፣ ህጻናት ያሏቸው ሴቶች እና ህሙማንን መታደግ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"ህዝባችን ለ 120 ቀናት እንደምንም መቆየት አለበት። ምክንያቱም እነዚያ የክረምት ቀናት ናቸው። የክረምት ወራት ናቸው። ሩሲያ የምትፈልገው ያንን ነው። በክረምቱ ወቅት በህዝባችን ላይ ከፍተኛውን ሰቆቃ መፍጠር ትፈልጋለች" ብለዋል።
ቬሬሽቹክ እንዳሉት ደቡባዊ ኼርሰንን ጨምሮ የዩክሬን አንዳንድ ክፍሎች አሁንም በየቀኑ የቦምብ ጥቃት እየተፈፀመባቸው ነው። የዩክሬን መንግሥት በፈቃደኝነት ከአካባቢዎቹ የማስለቀቅ ሥራ ጀምሯል።
የኼርሰን ክልል ባለስልጣናት እንዳሉት በከተማዋ ላይ በተፈጸሙ የሩስያ የሮኬት ጥቃቶች ሰባት ሰዎች ሲገደሉ 21ዱ ቆስለዋል።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ወሳኝ የሆኑ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ በማድረግ ሩሲያ የጦር ወንጀል እየፈፀመች ነው ሲሉ ደጋግመው ተናግረዋል። ሞስኮ ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቁት ሞስኮ በየካቲት 24 የጀመረችውን ጦርነት ለማስቆም የዩክሬን መሪዎች የሩሲያን ፍላጎት በማሟላት "በአካባቢው ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ስቃይ" ማስቆም እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ረዳት ሚካሂሎ ፖዶሊያክ በትዊተር ገጻቸው ለዚህ በሰጡት ምላሽ “በሰላማዊ ከተሞች ሚሳኤሎችን እያስወነጨፉ ስለሰላም ማውራት ከፍተኛ የስብዕና መዛባት ነው" ብለዋል።