ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተገለፀ
የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በሁለት ወራት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የታጣቂ እና የወንጀለኛ ቡድን አባላትን በቁጥጥር ስር ማድረጋቸውን መንግሥት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ዛሬ እንዳስታወቀው የሸኔ፣ የህወሓት፣ የአልሻባብ እና ሌሎች የወንጀል ቡድኖች አባላት እና በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ ግለሰቦችን መያዛቸውንና ሌሎች ላይ ደግሞ እርምጃ መወሰዱን አመልክቷል።
የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ እንዳለው በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በአስቸኳይ መከናወን አለባቸው ያላቸውን ተግባራት አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ ነው ተገኘ ያለውን ውጤት ይፋ ያደረገው።
በዚህም መሠረት በምዕራብ እና በደቡብ የአገሪቱ ክፍል እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረውና መንግሥት በሽብር ቡድንነት የሰየመው ሸኔ-የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት መካከል 3180 “በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ እጃቸውን ላለመስጠት አሻፈረኝ ያሉት ተደምስሰዋል” ብሏል።
በተጨማሪም ከ497 በላይ የህወሓት፣ የአልሻባብና ሌሎች አክራሪ ቡድኖች አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የተደራጁ ወንጀሎችን ሲመሩ ነበር የተባሉ 314 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም 75 የከተማ እና የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው መያዛቸውን አመልክቷል።
መግለጫው ጨምሮም በኦሮሚያ ክልል ሸኔን ለመደምሰስ የሚያስችሉ ናቸው የተባሉ የሸዋ፣ የወለጋ እና የጉጂ ኮማንድ ፖስቶች የተደራጁ መሆናቸውን ገልጾ፣ በዚህም የአገር መከላከያ፣ የክልሉ አመራርና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል።
በተወሰዱት እርምጃዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ከተባሉት የቡድኖቹ ታጣቂዎች በተጨማሪ፣ በርካታ የጦር መሳሪያዎች፣ ጥይቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ገንዘብ እና ልዩ ልዩ ንብረቶች በፀጥታ ኃይሎች መማረካቸውን ተጠቅሷል።
መግለጫው እንዳለው በጠላት ተይዘው እና ፈርሰው ነበሩ ከተባሉ 1,739 ቀበሌዎች መካከል 1,255 ያህሉ እንደገና መደራጀታቸውንና 252,129 የቤተሰብ አባላት ያሏቸው 47,558 አባዎራዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።
ተደጋጋሚ ጥቃቶች በታጣቂዎች በሚፈጸሙበት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልን በተመለከተም የደኅንነት ምክር ቤቱ እንዳለው “ያለው የስጋት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ፣ ሰላምና ደኅንነት ይበልጥ እየተረጋገጠ መምጣቱን” ገልጿል።
በክልሉ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሕገ ወጥ ታጣቂዎች የተደመሰሱ ሲሆን፣ 1,826 የሚደርሱ ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። 749 ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎች እና 5,639 ተተኳሾች ከጠላት የተማረኩ ሲሆን፣ 9 ጀልባዎችና 65 የጠላት ካምፖችም ወድመዋል።
እጃቸውን በሰላም የሰጡ ሕገወጥ ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ሕይወት የማስገባት እንዲሁም፤ በከማሺና በመተከል ዞኖች 171,485 ተፈናቃዮችን የማቋቋም ሥራ ተሠርቷል። ከጠላት ነጻ ከወጡ 180 ቀበሌዎች መካከል በ169ኙ የመንግሥት መዋቅር መልሶ ተደራጅቷል።
በአማራ ክልልም ሕግን ለማስከበር በተወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን አስታውሶ፣ ከመካከላቸው የፀጥታ ኃይሎችንየከዱ እና በልዩ ልዩ ወንጀሎች የሚፈለጉ እንዳሉበት ተጠቅሷል።
በአዲስ አበባ ከተማም ከፀጥታ፣ ከመልካም አስተዳደር እና ከሙስና ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች ለማስተካከል የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
በደቡብ ክልልም ስላለው የፀጥታ ሁኔታ ያነሳው ምክር ቤቱ፣ በክልሉ ሰላምንና ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና ከብሔረሰቦች የሚነሡ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ዘላቂ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም በሶማሌ ክልል በቅርቡ በአልሻባብ የተሰነዝውን ጥቃት አንስቶ በመከላከያ ሠራዊትና በክልሉ የፀጥታ ኃይል በተወሰደ እርምጃ 813 የቡድኑ አባላት ሲገደሉ 79ኙ መማረካቸው ተገልጿል።
ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እንዲፈታ መንግሥት መወሰኑን አመልክቶ፣ ድርድሩ ውጤት እስኪያመጣ ድረስ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ሁሉም ተረድቶታል ብሏል።
የኢትዮጵያብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ጨምሮም በቀጣይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ሐሳቦችን አስቀምጧል። በዚህም መሠረት “አሸባሪ እና ሕገ ወጥ ታጣቂዎችን ስጋት ከማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ” እንደሚገባ ጠቅሶ፣ ሕዝብን በማወያየት፣ የታጠቁ አካላትን በማግባባት፣ ወጣቶችን በሰላም ተግባራት ላይ በማሳተፍ፣ ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጡ ሥራዎችን እንደሚሰሩ ገልጿል።
እንዲሁምበተለያዩ ዘርፎች ለሰላም፣ ለፀጥታ እና ለመልካም አስተዳደርእንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ እርምጃ በመውሰድ የተለያዩ ዘርፎችን ጠቅሷል።