ፈረንሳይ ሰንደቅ ዓላማዬን ‘ዘልፈዋል’ ያለቻቸውን ቱኒዝያዊ ኢማም አባረረች

ማህጁብ ማህጁቢ

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock

ፈረንሳይ በአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ተገቢነት የሌለው አስተያየት ሰጥተዋል ያለቻቸውን ቱኒዝያዊ ኢማም ማባረሯን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒ ተናገሩ።

ማህጁብ ማህጁቢ የተባሉት ኢማም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በርካቶች ባጋሩት ቪዲዮ ላይ የፈረንሳይን ሰንደቅ ዓላማ ‘ሰይጣናዊ’ ሲሉ የጠሩት ይመስላል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዳርማኒ ፈረንሳይ በኢሚግሬሽን ሕጓ ላይ ያደረገችው ማሻሻያ ኢማሙን በፍጥነት ከአገር ለማስወጣት አስችሏል ብለዋል።

ኢማሙ በበኩላቸው ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈጸሙና የማንንም ክብር ዝቅ ለማድረግ እንዳላለሙ ተናግረዋል።

ትውልደ ቱኒዝያዊው ማህጁብ ማህጁቢ በፈረንሳይ ለ38 ዓመታት የኖሩ ሲሆን በደቡባዊ ፈረንሳይ በምትገኝ ባኞልስ ሱር ሴዜ በተሰኘች ትንሽ ከተማ ውስጥ ኤታአባ መስጊድ በኢማምነት ያገለግሉ ነበር።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ “ባለ ሦስት ቀለም ያለው ሰንደቅ ዓላማ” ሰይጣናዊ ነው፣ እንዲሁም “በአላህ ዘንድ ዋጋ የለውም” የሚሉበት ቪዲዮ መጋራቱን ተከትሎም ነው ኢማሙ በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ኢማሙ ምንም እንኳን ስለየትኛው ሰንደቅ ዓላማ እየተናገሩ እንደሆነ በትክክል ባይጠቅሱም በቪዲዮው ስር የተሰጡ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች የፈረንሳይ ሰንደቅ ዓላማን ማለታቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል። ኢማሙ በኋላ ላይ “አስቀይሜ ከሆነ አዝናለሁ” ያሉ ሲሆን ስለ ሰንደቅ ዓላማ የተናገሩትም “የምላስ ወለምታ” ነው ብለዋል።

ሐሙስ ዕለት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢማሙ ከአገር እንዲባረሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥ በመጠየቅ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈው የነበረ ሲሆን ፈረንሳይ የውጪ ዜጎችን ከአገር ለማባረር ያቀለላትን አዲሱን የኢሚግሬሽን ሕግም አወድሰዋል።

የፈረንሳይ ሚዲያ ኢማሙ የተባበሩበትን ትዕዛዝ ያተመ ሲሆን ይህም ኢማሙ “ጎታች፣ አለመቻቻልን እና አመጽን የሚያበረታታ የእስልምና ምስልንም በማስተዋወቅ ከፈረንሳይ ሪፐብሊክ እሴት ተጻርረዋል” ይላል።

የኢማሙ አስተምህሮት “በሴቶች ላይ የሚደርሱ መድልዎችን የሚያበረታታ፣ ከአይሁድ ማሕበረሰብ ጋር ያለውን ውጥረት የሚጨምር እና አክራሪነትን የሚያበረታታ” መሆኑም ተነግሯል።

በተጨማሪም የአይሁድን ማሕበረሰብ “ጠላት” ሲሉም ጠርተውታል በሚል የተባረሩበትን ትዕዛዝ አስፍሯል።

ኢማሙ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከ12 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲባረሩ ተደርገዋል።

ፈረንሳይ ያሻሻለችው የኢሚግሬሽን ሕግ የወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ወይም “ለሕዝብ ጸጥታ ከፍተኛ አደጋ ናቸው” ተብለው የተገመቱ የውጭ አገር ነዋሪዎችን በቀላሉ እንዲባረሩ ያዛል።

የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ማህጁብ ማህጁቢ ሐሙስ ምሽት ወደ ቱኒዝያ እንደበረሩ ዘግበዋል። የኢማሙ ጠበቃም ከአገር የመባረራቸውን ውሳኔ ይግባኝ እንደሚሉ ተናግረዋል።