የትግራይ አመራሮች የአፍሪካ ኅብረትን የድርድር ጥሪ መቀበላቸውን አስታወቁ

የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል

የፎቶው ባለመብት, DW

የትግራይ መሪዎች በአፍሪካ ኅብረት የቀረበላቸውን የሰላም ድርድር ጥሪ ግብዣ እንደሚቀበሉ አስታወቁ።

የትግራይ ክልል ረቡዕ መስከረም 25/2015 ዓ.ም. ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት በደቡብ አፍሪካ በሚደረገው የሰላም ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነን ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ረቡዕ ረፋድ የአፍሪካ ኅብረት ያቀረበውን የሰላም ድርድር ጥሪ ግብዣ ከመንግሥት የቀደመ አቋም ጋር የሚስማማ ነው በማለት መቀበሉን መግለጹ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል ተፈርሞ በወጣው እና ለኅብረቱ ሊቀ መንበር በተጻፈው ደብዳቤ የቀረበላቸውን የሰላም ድርድር ግብዣ እንደተቀበሉ ገልጾ፣ ድርድሩ አመርቂ ጅምር እንዲኖረውም አንዳንድ ማብራሪያዎችን ጠይቋል።

በዚህ የሰላም ውይይት ላይ ተሳታፊዎች፣ ታዛቢዎች እና ዋስትና ሰጪዎች ተጋብዘው እንደሆነ እና የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ስለሚኖረው ሚናን በተመለከተ ኅብረቱ ማብራሪያ ይሰጠን ብለዋል።

የሰላም ውይይቱ ጥሪ የትግራይ አመራሮችን ያላማከረ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ በተጨማሪ ትግራይ ለምትልከው ተደራዳሪ ቡድን፣ ጉዞ የደኅንነት ዝግጅቶችን እና ሎጂስቲክስን በተመለከተ ኅብረቱ ምን እንዳሰበ ጠይቋል።

ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በተላከው በዚህ ደብዳቤ “ጦርነቱን ማቆም የኅብረቱ ዋና አጀንዳ አካል መሆኑን ማወቅ ለሰላም ሂደቱ ጠቃሚ ይሆናል” ብሏል።

የአፍሪካ ኅብረት መስከረም 21/2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤና በአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ተፈርሞ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለህወሓት ሊቀ መንበር ደብረ ጽዮን በተላከው የሰላም ድርድር ግብዣ መሠረት እሁድ መስከረም 29/2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ በታቀደው “የሰላም ውይይት” ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአፍሪካ ኅብረት “በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚካሄደው ይህ የሰላም ውይይት ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት መሠረት የሚሆኑ መርሆች፣ የአጀንዳ ጉዳዮች፣ አሰራሮች እና የጊዜ ሰሌዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል” ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም የሰላም ውይይቶች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ብቻ እንዲሆኑ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታም እንዲጀመር መግለጹ ይታወሳል።

“በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ለመነጋገር ዝግጁ ነን። ውይይቶቹ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታዎች መጀመር አለባቸው” ብሎ ነበር።

የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም ለኅብረቱ መስከረም 01/2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የሚካሄደውን የሰላም ውይይት እንደሚቀበልና ጦርነቱን በአስቸኳይ እና በድርድር ላይ ተመስርቶ ግጭት ለማቆም ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር።

በዚህም የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ የሆኑትን አቶ ጌታቸው ረዳን እና የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤን በአደራዳሪነት መሾማቸው ተገልጾ ነበር።

ለአምስት ወራት የዘለቀው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ጦርነቱ ካገረሸ በኋላ ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ለማደራደር ይህ የአፍሪካ ኅብረት ጥሪ የመጀመሪያው ይፋዊ ሙከራ ነው።

በባለፉት ሳምንታት ከሳተላይት የተነሱት ምስሎች ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ከፍተኛ የጦር ሠራዊት ክምችት እና መሳሪያዎች የተጠመዱባቸውን ቦታዎች አሳይተዋል።

ከሰሞኑ ኤርትራ ተጠባባቂ ጦሯን ለክተት በማዝመት ትግራይ ውስጥ ጥቃት መፈጸሟ ሪፖርት ተደርጓል።

ጋብ ብሎ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት እንደገና ማገርሸቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ በአስከፊ ደረጃ መባባሱን የአውሮፓ ኅብረት ከሰሞኑ አስታውቋል።

በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች 13 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እርዳታ ፈላጊ እንደሆነ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።