ቦክሰኛዋ ኢማን ኸሊፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ጥቃት ኤለን መስክና ጄኬ ሮሊንግን ከሰሰች

ኢማን ኸሊፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢማን ካሸነፈች በኋላ በፆታ ማንነቷ ላይ የተቃጡ የበይነ መረብ ጥቃቶች ብርታት ሰጥተዋት ቻይናዊቷ የዓለም ሻምፒዮን ያንግ ሊን እንዳሸነፈች ተናግራለች።

አልጄሪያዋቷ ቦክሰኛ ኢማን ኸሊፍ በፓሪስ ኦሊምፒክ ወቅት በበይነ መረብ ጥቃት አድርሰውብኛል በማለት ኤለን መስክ እና ጄኬ ሮሊንግን በክስ ውስጥ አካተተች።

በፓሪስ ወርቅ ያገኘችው ቦክሰኛዋ አምና የፆታ መመዘኛ ምርመራ አላለፈችም በሚል በዓለም አቀፍ የቦክስ ማኅበር ከውድድር ውጭ መደረጓ ይታወሳል።

ሆኖም ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ኢማን መወዳደር እንደምትችል ወስኗል።

ጠበቃዋ ነቢል በውዲ እንዳሉት፣ ኤለን መስክ እና ጄኬ ሮሊንግ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት አስተያየት ክስ ውስጥ ይካተታሉ።

ኢማን በፓሪስ ኦሊምፒክ አነጋጋሪ ሆና ነበር። በተለይም ጣልያናዊቷ ቦክሰኛ አንጀላ ካራኒ ከውድድሩ በ46 ሰኮንድ ከወጣች በኋላ ከፆታ ማንነት ጋር በተያያዘ ኢማን መነጋገሪያ ሆናለች።

የፓሪስ ዐቃብያነ ህግ ለኤኤፍፒ እንደገለጹት፣ የኢማንን ጥቆማ ተከትሎ የማኅበራዊ ሚዲያ ጥቃት ላይ ምርመራ ጀምረዋል።

አንድ ታዋቂ የፈረንሳይ ጠበቃ ኤለን መስክ እና ጄኬ ሮሊንግ ይቀጣሉ ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።

የፈረንሳይ ሕግ ከፈረንሳይ ውጭ የተደረጉ ወንጀሎችን አይቀጣም።

ሆኖም ፈረንሳይ ሳሉ መልዕክት ያስተላለፉ ሰዎችን ክሱ ይመለከታል።

አምና ከውድድር ታግደው የነበሩት ኢማን እና ታይዋናዊቷ ሊን ዩ-ታንግ በሴቶች የቦክስ ውድድር እንዲሳተፉ ይሁንታ አግኝተዋል።

ዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ለሁለቱ ሴቶች መብት ተከራክሮ ውሳኔውን ቀልብሷል።

የኮሚቴው ፕሬዝዳንት ቶማስ ባክ “ይህ የፍትሕ ጥያቄ ነው። ሴቶች በሴቶች ውድድሮች እንዲሳተፉ መፈቀድ አለበት። ሁለቱም ሴቶች ናቸው” ብሏል።

የኤክስ ዋና ኃላፊ ኤለን መስክ እና የ ‘ሀሪ ፖተር’ ደራሲ ጄኬ ሮሊንግ ስለ ቦክሰኛዋ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።

ደራሲዋ “ጭንቅላቷን የመታት ሴት ላይ ያሳደረውን ጫና እያየ ይደሰታል” ስትል ኢማን ጣልያናዊቷን ቦክሰኛ ድል ካደረገች በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽፋለች።

ኤለን መስክ በዋናተኛው ሪሌይ ጌይንስ የተጻፈ “ወንዶች በሴቶች ስፖርት መግባት የለባቸውም” የሚል መልዕክት አጋርቷል።

ቢቢሲ ከሁለቱም ግለሰቦች ተወካዮች አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቦ ምላሻቸውን እየጠበቀ ነው።

ኢማን ካሸነፈች በኋላ በፆታ ማንነቷ ላይ የተቃጡ የበይነ መረብ ጥቃቶች ብርታት ሰጥተዋት ቻይናዊቷ የዓለም ሻምፒዮን ያንግ ሊን እንዳሸነፈች ተናግራለች።

ጄኬ ሮሊንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ደራሲዋ “ጭንቅላቷን የመታት ሴት ላይ ያሳደረውን ጫና እያየ ይደሰታል” ስትል ኢማን ጣልያናዊቷን ቦክሰኛ ድል ካደረገች በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽፋለች።

የ25 ዓመቷ ቦክሰኛ “በውድድሩ ለመሳተፍ ብቁ ነኝ። ሴት ሆኜ ነው የተወለድኩት። ሴት ሆኜ ነው የኖርኩት። የተወዳደርኩትም ሴት ሆኜ ነው” ብላለች።

ጣልያናዊቷ ቦክሰኛ ውድድሩን ከተሸነፈች በኋላ የኢማንን እጅ አልጨብጥም በማለቷ ይቅርታ ጠይቃለች።

ስለ ፆታ ማንነት የሚደረገውን ምርመራ በተመለከተ ዓለም አቀፍ የቦክስ ማኅበር በግልጽ መረጃ ባይሰጥም አምና ሁለቱን ሴቶች ከውድድር ውጭ አድርጓል።

በዚህ ውድድር ምን እንደሚካተት ቢቢሲ ለማወቅ አልቻለም።

በሩሲያ የሚመራው ዓለም አቀፍ የቦክስ ማኅበር እአአ በ2019 በዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ብቁ አይደለም በሚል ዕውቅና ተነፍጓል።