ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ቀናቸው ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች የትኞቹ ናቸው?

47ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በጨበጡ ዕለት በርካታ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል።

ፕሬዝደንቱ የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ሕግ የመሆን ኃይል ቢኖራቸውም በመጪ ፕሬዝደንት ሊሻሩ አሊያም በፍርድ ቤት ሊቀለበሱ ይችላሉ።

የትራምፕ አብዛኛዎቹ ውሳኔ በፍርድ ቤት ሊታገዱ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

እነሆ ትራምፕ በሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያው ቀን ያስተላለፏቸው ትዕዛዞች።

ስደተኞችን በተለመከተ

በድንበር አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ትራምፕ ከኦቫል ኦፊስ ያስተላለፉት ትዕዛዝ በአሜሪካ ድንበር አካባቢ አስቸኳይ ጊዜ እንዲታወጅ ያትታል።

ፕሬዝደንቱ ፊርማቸውን ከማሳረፋቸው በፊት "ይሄማ ትልቅ ውሳኔ ነው" ብለዋል።

ሕጋዊ ወረቀት ኬላቸው ወላጆች የሚወለዱ ልጆች አሜሪካዊ ዜግነት እንዲያገኙ የሚያስችለው ሕግ እንዲሰረዝም ወስነዋል።

ለሚቀጥሉ አራት ወራት የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም አይኖርምም ብለዋል። ነገር ግን የዚህ ውሳኔ ዝርዝር ግልፅ አይደለም።

ድንበር መዝጋት

ትራምፕ ጦር ሠራዊቱ "ድንበሩን እንዲዘጋ" አዘዋል። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት ያስቀመጡት አደገኛ የዕፅ ዝውውር፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ወንጀለኞች ድንበር ጥሰው መግባታቸውን ነው።

ዕፅ አዋዋሪዎችን ሽብርተኛ ብሎ መፈረጅ

ፕሬዝደንቱ የፈረሙበት መመሪያ አደገኛ ዕፅ የሚያዘዋውሩ ቡድኖች እና ዓለም አቀፍ ወንበዴዎችን የውጭ ሽብርተኛ ድርጅቶች ሲል ይፈርጃል።

የሳልቫዶሩ የሰዎች አዘዋዋሪ ቡድን ኤምኤስ-13 እና የቬንዙዌላው ትሬን ዴ አርሁዋ ከአል ቃኢዳ፣ ኢስላሚክ ስቴት እና ሐማስ ጋር ሽብርተኛ ተብለው ተፈርጀዋል።

አጥር ግንባታ

በሜክሲኮ እና አሜሪካ ድንበር አስቸኳይ ጊዜ ያወጁት ትራምፕ "በደቡባዊው ድንበር ተጨማሪ አጥር እንዲገነባ" ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ይህ ውሳኔ የመጨረሻ አይደለም። አጥር ለመገንባት በጀት ከየት ያመጣሉ የሚለውም ግልፅ አይደለም።

ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2016 ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመረጡ በሜክሲኮ እና አሜሪካ ድንበር አጥር ለመገንባት ውሳኔ አሳልፈው ነበር።

ምንም እንኳ የአጥር ግንባታው ቢጀመርም አብዛኛው ክፍል ሳይጠናቀቅ ነው ከሥልጣን የወረዱት።

ቲክቶክ

ትራምፕ ቲክቶክ ለሚቀጥሉት 75 ቀናት ከእገዳ ነፃ የሚሆንበትን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ቲክቶክ የትራምፕን ውሳኔ አመስግኖ ተቀብሏል። መተግበሪያው ለሰዓታት አሜሪካ ውስጥ መሥራት አቁሞ የነበረ ሲሆን ነገር ግን አሁን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ትራምፕ በውሳኔያቸው እንዳሉት የእፎይታ ጊዜ የቲክቶክ እናት ኩባንያ የአሜሪካ አጋር እንዲፈልግ ጊዜ የሚሰጥ ነው። የመመሪያው ዝርዝር ይፋ አልሆነም።

ከዚህ ቀደም ቲክቶክ መዘጋት አለበት የሚለውን ሐሳብ የደገፉት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በርካታ ሰዎች ቲክቶክን ተጠቅመው እንዳይዋቸው በመናገር አቋማቸውን ቀይረዋል።

የመንግሥት ክለሳ

ዶጅ እና ኢላን መስክ

ትራምፕ የመንግሥት ወጭ ቅነሳን የሚቆጣጠር ዲፓርትመንት ኦፍ ገቨርንመንት ኤፊሸንሲ አሊያም ዶጅ የተባለ መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ይህ የመንግሥት ወጭን ይቆጣጠራል የተባለ መሥሪያ ቤት በቢሊየነሩ ኢላን መስክ የሚመራ ይሆናል።

ትራምፕ እንዳሉት የስፔስኤክስ እና ቴስላ ባለቤት መስክ 20 ገደማ ሠራተኞችን ቀጥሮ የሚያስተዳድርበት ቢሮ ይሰጠዋል።

የፌዴራል ቅጥር መቋረጥ

ትራምፕ የፈረሙበት ትዕዛዝ ማንኛውም የፌዴራል መሥሪያ ቤት ቅጥር ለጊዜው እንዲቆም ያዛል። ጦር ሠራዊቱ እና አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ግን ቅጥር ማከናወን ይችላሉ።

ትራምፕ የእሳቸው አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ሥልጣን እስኪቆጣጠር ድረስ ነው ቅጥር እንዲቆም ያዘዙት።

አክለው የፌዴራል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ከዚህ በኋላ ከቤት መሥራት አይችሉም የሚል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይህ ማለት ሠራተኞቹ ወደ ቢሮ መግባት ግዴታ ይሆንባቸዋል ማለት ነው።

ሳንሱር

ትራምፕ ሌላ ያስተላለፉት ውሳኔ "የንግግር ነፃነትን የሚመለስ እና የመንግሥት ሳንሱርን የሚከላከል" ነው። ይህ ውሳኔ ምን ማለት ነው ስለሚለው ዝርዝር መረጃ አልወጣም።

ነገር ግን ውሳኔው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፍትሕ ሚኒስቴርና ሌሎች ኤጀንሲዎችን ሥራ እንዲመረምር ኃላፊነት ይሰጣል።

የዓለም ጤና ድርጅት

ትራምፕ አገራቸው ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት የመውጣት ሒደት የምትጀምርበትን ትዕዛዝም አስተላልፈዋል።

ፊርማቸውን ከማሳረፋቸው በፊት "ኧረ! ይህማ ትልቅ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ድርጅቱ የኮቪድ ወረርሽኝን በአግባቡ አልተወጣም ብለው የሚወቅሱት ትራምፕ በመጀሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ከድርጅቱ አባልነት መውጣታቸው አይዘነጋም። ነገር ግን የባይደን አስተዳደር ይህን ውሳኔ ቀልብሶታል።

የፆታ ጉዳይ

ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በኋላ አሜሪካ ሁለት ፆታዎችን ብቻ ነው የምትቀበለው፤ አኒህም "ወንድ እና ሴት ናቸው" ብለዋል።

ይህ ውሳኔያቸው የመንግሥት ግንኙነት፣ የሲቪል መብት ጥበቃዎችን፣ የፌዴራል በጀት ጉዳይ እና እስር ቤቶችን የሚመለከት ይሆናል። ፓስፖርት እና ቪዛ ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይገመታል።

በሌላ ትዕዛዝ ደግሞ "ብዝሀነት፣ እኩልነት እና አካታችነት" አሊያም ዲኢአይ እየተባለ የሚጠራውን ፖሊሲ መሻራቸውን አስታውቀዋል።

ሌሎች የትራምፕ ውሳኔዎች

  • የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤን የአሜሪካ ባሕረ ሰላጤ ብሎ መሰየም
  • የዋጋ ግሽበትን መከላከል
  • የባይደን ፖሊሲዎችን መሻር
  • ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መውጣት
  • የኢነርጂ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
  • በካፒቶል አመፅ ለተሳተፉ ሰዎች ይቅርታ ማድረግ ይገኙበታል