ላጤ እናት፡ የኢትዮጵያውያን ላጤ እናቶች ምርጫ እና ተግዳሮት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመላው ዓለም የላጤ ወላጆች ቁጥር እየጨመረ ነው።
አሜሪካ ልጆች ከነጠላ ወላጃቸው ጋር የሚኖሩባት ከዓለም ቀዳሚዋ አገር ናት። እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በተካሄደ የሕዝብ ቆጠራ መረጃ መሠረት ከ10 ሚሊዮን በላይ አሊያም አንድ አራተኛ የሚሆኑት አሜሪካውያን ልጆች የሚኖሩት ከአባታቸው አሊያም ከእናታቸው ጋር ነው።
'ኢኮኖሚክ ኮኦፕሬሽን ኤንድ ደቨሎፕመንት' በተባለ ድርጅት በተሠራው ጥናትም በነጠላ ወላጅ የሚመሩ ቤተሰቦች ቁጥር አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ኦስትሪያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቱርክ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በ38 አባል አገራቱ እንደሚጨምር አመልክቷል።
ለዚህም በተለይ በአውሮፓ እና እስያ አገራት የፍቺ መበራከት፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንዲሁም የሴቶች የሥራ ተሳትፎ መጨመር በዋና ምክንያትነት ተጠቅሷል።
በአውሮፓውያኑ 2023 የተሠራ እና 'ፖፕሌሽን አሶሲየሽን ኦፍ አሜሪካ' በተባለ ድረገጽ ላይ የታተመ አንድ ጥናት በአፍሪካ ያላገቡ እናቶች ቁጥር አዲስ የቤተሰብ መልክ እየሆነ መምጣቱን አሳይቷል።
ጥናቱ ካሳተፋቸው እና ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 49 ሆነው ያላገቡ 36 ሺህ 122 እናቶች መካከል 22.4 በመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች እናቶች ናቸው።
ከእነዚህ 8 ሺህ 73 ላጤ እናቶች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ወይ 37 በመቶዎቹ በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆን ዝቅተኛው 16 በመቶ ደግሞ በመካከለኛው አፍሪካ የሚኖሩ ናቸው።
በደቡብ አፍሪካ ከ50.5 በመቶ በላይ የሆኑ ያላገቡ ነጠላ እናቶች ናቸው።
ምንም እንኳን የተሠሩ ጥናቶች ባለመኖራቸው ቁጥራቸው እና የጉዳዩ ስፋት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ባይቻልም በኢትዮጵያ በተለይ በከተሞች አካባቢ ላጤ እናትነት አንዱ የሕይወት ዘይቤ እየሆነ ነው።
እነዚህ ሴቶች ላጤ እናት (Single Mother) የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች ነው። ከእነዚህም መካከል ከአጋራቸው ጋር በሞት አሊያም በፍቺ መለያየት፣ በተፈፀመባቸው ጥቃት ሳቢያ የልጅ እናት ለመሆን መገደድ እንዲሁም የጀመሩት ግንኙነት እንዳሰቡት አለመስመር ይጠቀሳሉ።
ነገር ግን ፈልገውና አቅደው፤ ልጅ ብቻ እንዲኖራቸው በማለም ላጤ እናት (Single Mother) የሚሆኑ ሴቶችም አሉ።
ሴቶች አስበውና አቅደው ለምን ላጤ እናት ይሆናሉ?
"በሕይወቴ ያሰመርኩት ቀይ መስመር ነበር፤ እርሱን ማለፍ ስለማልችል ላጤ እናት ሆኛለሁ" ብላለች ቢቢሲ ያነጋገራት አንዲት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ። ስሟን ያልጠቀስናት ይህች እናት ለትዳር ክብር እንዳላት አልሸሸገችም።
በሕይወቷ የምታስበው እና የምታልመው ስላልሆነ የግድ በትዳር መታሰር የለብኝም የሚል አቋም ላይ እንደደረሰች ትናገራለች።
ይሁን እንጂ ላጤ እናት መሆን በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉት ታነሳለች።
የሴቶች መብት ተሟጋቿ አክሊል ሰለሞን በበኩሏ እያንዳንዷ ሴት በሰውነቷ ላይ እንዲሁም በምትመሰርተው ቤተሰብ ላይ ውሳኔዎችን ትወስናለች። ውሳኔዋም እንደምትኖረው ሕይወት የተለያየ ነው የሚሆነው" ስትል ከዓመታት በፊት ቢቢሲ ባነጋገራት ወቅት ተናግራለች።
ተሟጋቿ ሴቶች ፈልገውና አቅደው ላጤ እናት የሚሆኑባቸውን ምክንያቶችንም ትጠቅሳለች። በማኅበረሰቡ የሴት ልጅ ሕይወት በጊዜ የተገደበ እንደሆነና እስከተወሰነ ዕድሜያቸው ድረስ ማግባት እና መውለድ ካልቻሉ ሕይወታቸው እንደተመሳቀለ ተደርጎ መወሰዱ ለእንዲህ ዓይነት ውሳኔ ከሚገፏቸው ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ትናገራለች።
በሌላ በኩልም እየታየ ያለው የማኅበረሰብ አመለካከት ለውጥ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የራሱ የሆነ ድርሻ አለው።
አክሊል እንደምትለው በቀደመው ጊዜ አንዲት ሴት ሳታገባ ብትወልድ ለልጁ 'ዲቃላ' የሚል ስያሜ በመስጠት እናትየዋ ትወገዝ ነበር። አሁን ላይ ግን ይህ ልማድ በትንሹም ቢሆን እየቀረ በመሆኑ ሴቶች እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያሳልፉ አደፋፍሯቸዋል።
"ከዚህ ቀደም ሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኛ በሆኑበት ጊዜ ልጅ ወልደው ለብቻቸው ማሳደግ የማይታሰብ ነበር" የምትለው አክሊል የሴቶች የኢኮኖሚ አቅም ማደግም ሌላኛው የላጤ እናትነት ምክንያት እንደሆነ ትገልጻለች።
እንደ የመብት ተሟጋቿ ከሆነ አንዲት ሴት ያየችው የትዳር ሕይወት እኩልነት የሌለበት፣ ሴቷ ጥገኛ የሆነችበት፣ ጥቃት የሚፈፀምበት፣ የኃይል ሚዛኑ እኩል ያልሆነበት እንዲሁም ሁኔታዎች በሙሉ ለሴት የማይመቹ ከሆኑ ይህን ባለመፈለግ ላጤ እናትነትን ትመርጣለች።
ቢሆንም ግን ጤናማ ትዳርን እያዩ ያደጉትም ሌሎች ምክንያቶች ወደ ውሳኔው ሊያንደረድሯቸው ይችላሉ።
አሁን ላይ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ የሴቶች የኢኮኖሚም ይሁን የትምህርት አቅም እየጎለበተ ቢመጣም ሴቶች አቅማቸውን እና የትዳር ሕይወታቸውን ማጣጣም ተስኗቸዋል የሚሉ እንዳሉ ያነሳንላት አክሊል "የሴቶች አቅም እየጎለበተ በመጣ ቁጥር ኃላፊነት እየተደራረበባቸው ነው የመጣው። የቤቱን ሳንቀንስ ነው የውጪውን የጨመርንባቸው" ስትል ትሞግታለች።
ሆኖም ላጤ እናት መሆንም ይህንን ጫና አያስቀረውም ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአሃ የሥነ ልቦና አገልግሎት አማካሪ የሆኑት አቶ ሞገስ ገ/ማሪያም በበኩላቸው "ይህ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚታይ ልማድ ሆኗል" ይላሉ።
የምክር አገልግሎት ፈልገው ወደ እርሳቸው የሚመጡ ላጤ እናቶች መኖራቸውንም ይገልፃሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት ጉዳዩ ከሥልጣኔ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። የኢኮኖሚና በራስ የመተማመን አቅም ሲያድግ የባል እና የሚስት ግንኙነት ወደ ጎን ተትቶ ግንኙነቱ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል።
በዚህም ምክንያት ሌሎች ማኅበራዊ፣ አካላዊ፣ መንፈሳዊ እሴት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደማያስፈልግ አሊያም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ተወስዶ ሴቶች ላጤ እናትነትን "በፍላጎት" ይመርጣሉ።
ለዚህም "እኔ በኢኮኖሚ ጥሩ ደረጃ ላይ ስለደረስኩኝ፤ ከመጀመሪያውም ጀምሮ የወሰንኩት ሳላገባ ልጅ ለመውለድ ነው" ያለቻቸውን ደንበኛቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
እንዲህ ዓይነት ሃሳቦች የባልን (የትዳር አጋርን) ሚና እና ትርጉም ከማዛባት ጋር የተያያዘም ነው ይላሉ - አቶ ሞገስ።
ባለሙያው እንደሚያስረዱት ላጤ እናትነትን ከኢኮኖሚ ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም። ጉዳዩ ከራስ ስሜት እና አስተሳሰብ ጋር እንዲሁም ካለፈ ታሪክ ጋር የሚገናኝም ነው። በመሆኑም ገፊ ምክንያቶቹን ውስጣዊ እና ውጫዊ በማለት ይለዩታል።
ለአንድ ውሳኔ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የውስጥ ሁኔታ ነው ይላሉ- የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ ሞገስ።
"ለራሳችን ያለን የጠነከረ አስተሳሰብ (Ego) እና ለራስ የምንሰጠው ግምት ከመጠን ያለፈ ሲሆን (Super Ego) ነገሮችን ሁሉ እኔ ማድረግ እችላለሁ፤ እኔ ማድረግ የምችል ከሆነ ሌላ አያስፈልገኝም የሚል ስሜት ይመጣል። በመሆኑም ይህንን ሚዛናዊ ማድረግ ካልተቻለ እዚህ ውሳኔ ላይ በቀላሉ ይደረሳል" ይላሉ።
ይህ የውስጥ ሁኔታ የውጫዊ ተፅዕኖ ነፀብራቅም ይሆናል። ለምሳሌ የቤተሰብ፣ የጎረቤት ወይም በዙሪያችን ያሉ ሁኔታዎች የሚያሳድሩት ተፅዕኖ የውስጥ ውሳኔ ላይ ያደርሳሉ።
ፆታን መሠረት ያደረጉ የሕብረተሰብ አመለካከቶች፣ የሚፈፀሙ ጥቃቶች፣ የሚደርስባቸው ጫና፣ ሚዛናዊ ያልሆነ ሚና እንዲሁም የወንዶች የበላይነትን በመጥላት እና በመፍራት ሴቶች እዚህ ውሳኔ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ አቶ ሞገስ ያስረዳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢያቸው ያሉ ወይም በሚዲያ የሚሰሟቸው እና የሚያዩዋቸው አርአያዎች ተፅዕኖ ሊፈጥሩባቸው ይችላሉ።
በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ በጉዳዩ ላይ ያለው አቋም ጠንካራ ካልሆነ ሴቶች ውስጣቸው የሚጠይቃቸውን ለማድረግም ዕድሉን ያገኛሉ።
"የራስ ማንነት እያሸነፈ ሲመጣ አይሆንም የምንላቸው ነገሮች እየበዙ ይመጣሉ። ፍላጎታችንን ማስቀደም ይቀናናል" በማለትም ላጤ እናትነት የማኅበረሰቡ እሴት እንደተሸረሸረ አንዱ ማሳያ ሊሆን እንደሚችልም ባለሙያው ያክላሉ።
ላጤ እናት መሆን የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው?
ያነጋገርናት እናት እንደምትለው ልጆችን ለብቻ ማሳደግ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እና የሥነ ልቦና ጫና አለው። ከማኅበረሰቡ፣ ከቅርብ ቤተሰብ እንዲሁም ከልጆች የሚደርሰው ጫናም ቀላል አይደለም።
"ልጆቸ ራስ ምታት እንኳን ሲያማቸው የማካፍለው ሰው አለመኖሩ በጣም ከባድ እንደሆነ ተመልክቸዋለሁ፤ ግን የራሴ መርኅ ስላለ እርሱን መታገስ እና እንደ 'እናቶቻችን መቻል ስለማልችል' ላጤ እናትነትን መርጫለሁ" ትላለች።
ይህች እናት አዘውትረው ከሚጠቀሱት ጫናዎች በዘለለ የወሲብ ሕይወትን ማጣትም ላጤ እናትነትን እንደሚፈትን ትናገራለች።
ምንም እንኳን እያንዳንዱ ሰው የየራሱ ወሲባዊ ሕይወት ቢኖረውም እርሷ ግን ከሕይወት አጋር ውጪ ወሲብ መፈፀም እንደማትፈልግ ትገልጻለች።
የመብት ተሟጋቿ አክሊልም ላጤ እናት መሆን 'የሚያሳፍር ድርጊት ነው' ተብሎ በሚቆጠርበት ማኅበረሰብ ውስጥ በፍላጎት ላጤ እናት መሆን ማኅበራዊ ጫናው ከፍተኛ እንደሆነ ታስረዳለች።
"እነዚህን እናቶች የሚያግዝ አሠራር ከሌለ በስተቀርም ሁሉም ነገር በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ብቻ ስለሚወድቅ ኃላፊነቱ ከባድ ይሆናል" ትላለች።
በመሆኑም የኢኮኖሚ ጫናውም ቀላል አይሆንም፤ ይህንን ለማስተካከል ሥራ መስራት እና ጊዜን ሥራ ላይ ማጥፋት ይጠይቃል።
"የልጆች ኃላፊነት መደረብም ሁኔታውን ከባድ ያደርገዋል" የምትለው አክሊል፤ በዚህ ሂደት ውስጥ እናትየዋ ለእረፍት ማጣት ስለምትጋለጥ በተለያየ መልኩ ልትጎዳ እንደምትችል ታስረዳለች። ዳፋውም ለልጆቹ ይተርፋል።
በወላጆች ላይ ያለው ተጽእኖ
የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ ሞገስም ይህንን የተመለከቱ ጥናቶች በአፍሪካ ብዙም ባይኖሩም ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው ይላሉ። ጫናው ከአካላዊ፣ ከማኅበራዊ፣ ከመንፈሳዊ እና ከኢኮኖሚያዊ ደኅንነት (wellbeing) ይጀምራል።
በመሆኑም ላጤ እናቶች ካገቡት ይልቅ ለተለያዩ ቀውሶች ሊዳረጉ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል፡-
- ኢኮኖሚያዊ ጫና ይበረታባቸዋል
- አካላዊ ጤንነታቸው ጭንቀትን ከመቋቋም እና ከበሽታ መከላከል አንፃር ይዳከማል
- የስሜት ጥንካሬ እና መረጋጋት አይኖራቸውም
- ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ድጋፋቸውም የላላ ይሆናል
- ከሥነ ልቦና አንፃር ብቸኝነት፣ ድባቴ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ዋጋ የለኝም ማለት፣ በራስ መተማመን ማጣት እና ለማንነት ችግር መጋለጥ
አቶ ሞገስ እንደሚሉት ሚናቸው ምንም ይሁን ምን የልጆቹ አባቶችም ከሴቶቹ ባልተለየ መልኩ የችግሮቹ ተጋሪ ይሆናሉ።
ለስሜት ጫና፣ ለድባቴ፣ ለማኅበራዊ ጫና፣ ለጥፋተኝነት ስሜት፣ ለምቾት ማጣት እንዲሁም ልጄን በሚገባው መልኩ ድጋፍ እና ክትትል እያደረኩለት አይደለም ለሚል የፀፀት ስሜት ይዳረጋሉ።
አባቶች፤ ልጆቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ከአጠገባቸው ማጣት ብቻም ሳይሆን ገና ለገና እንፋታለን ብለው ሲያስቡ ሚዛናቸውን ወደ መሳት እና ከፍ ወዳለ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንደሚገቡም ባለሙያው ያክላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በልጆች ላይስ ምን ተጽእኖ ያሳድራል?
"በተለይ ልጆች ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ለብቻ ማስተዳደር ፈታኝ ነው" የምትለው ላጤ እናት በቤት ውስጥ ኃላፊነትን በማከፋፈል በሕይወታቸው ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ ፈተናውን መቋቋም እንደቻለች ትናገራለች።
"ቤታችን ፓርላማ ይመስላል፤ ልጆቼ ተነጋግረው ወስነው ወደ እኔ የሚመጡት ለማፅደቅ ነው፤ በሁሉም ነገር ተሳታፊ ናቸው" ትላለች።
ይህም ይበልጥ ጠንካራ እንዳደረጋቸው እና ሴት ብቻዋን ልጆች ማሳደግ እንደምትችል እርሷን እንደ አርአያ ማየት እንደጀመሩ ታስረዳለች። በተለይ ወንድ ልጇ በእርሷ ኩራት እንደሚሰማው ትናገራለች።
በትዳር ውስጥ ሆኖ ልጆችን በተገቢው መንገድ ማሳደግ መተኪያ እንደሌለው የምትናገረው ይህች እናት፤ ትዳር ለመያዝ ተብሎ አሊያም ጤናማ ያልሆነ ትዳር ውስጥ ሆኖ ሕይወትን በመግፋት ግን አታምንም።
የሴቶች መብት ተሟጋቿ አክሊልም ቤተሰብ የሚባለው ትርጓሜ ከድሮው በተሻለ ተቀይሯል በማለት "ልጆች የአባት እና የእናትን ሚና ካለማግኘት በበለጠ ማኅበረሰቡ የሚያደርስባቸው ጉዳት ያይላል" ትላለች።
አቶ ሞገስ ግን በዚህ አይስማሙም። ልጆች የአባታቸውን እና የእናታቸውን ሚና እያዩ ባለማደጋቸው ለተለያዩ የሥነ ልቦና ችግሮች እንደሚዳረጉ ያስረዳሉ። በመሆኑም እነዚህ ልጆች ድብርት እና ጭንቀት እንዲሁም ባህሪያዊ የሥነ ልቦና ችግሮች ይታዩባቸዋል ይላሉ።
እንደ ባለሙያው ገለፃ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በብዛት ለእንዲህ ዓይነት የሥነ ልቦና ችግር የሚዳረጉ ሲሆን፣ የሚያጋጥማቸውም 'ክሊኒካል' የሚባለው የሥነ ልቦና ችግር ነው።
ወንዶች ደግሞ ባህሪያዊ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ከሁኔታዎች ጋር ተስማምቶ መኖር ይቸግራቸዋል።
ችግሮቹ እንደ እናቶቹ ባህሪይ የሚወሰን ቢሆንም በትምህርት፣ በሥራ እና በማኅበራዊ ስኬቶቻቸው ላይ ተጽእኖ ያሳድርባቸዋል ብለዋል።
አቶ ሞገስ ላጤ እናቶች ሁለት ባህሪይ አላቸው ይላሉ። አንደኛው ልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ጥሩ ድርሻ ያላቸው፣ ፍቅር እና እንክብካቤ በጥሩ ሁኔታ የሚሰጡ (Involved) ሲሆኑ፣ ሌላኛው ደግሞ ልጆቻቸውን ችላ የሚሉ እና በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ የማይገቡ (Rejecting) ናቸው።
ይሁን እንጂ በሁለቱ የተለያየ ባህሪይ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ለተለያዩ ሥነ ልቦና ችግሮች መዳረጋቸው አይቀርም። ጥሩ ድርሻ ያላቸው እናቶች እንክብካቤ እና ፍቅራቸው ከልክ ያለፈ ስለሚሆን ልጆች ለጥገኝነት መንፈስ ይጋለጣሉ።
በሌላ በኩል ግድ የለሽ በሆኑት እናቶች የሚያድጉት ደግሞ ማግኘት ያለባቸውን የስሜት ደኅንነት ስለማያገኙ ቀደም ብለው ለተጠቀሱት የሥነ ልቦና ችግሮች ይዳረጋሉ።
ለምክር አገልግሎት ወደ እርሳቸው ቢሮ ጎራ ከሚሉት ላጤ እናቶች አብዛኞቹ ስሜታቸው ተመሳሳይ መሆኑን እና ልጆቻቸው ላይም የድብርት ስሜት ማየት እንደቻሉ ባለሙያው ጠቅሰዋል።
የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች እንዴት ይፍቱ?
ጤናማ ትዳር በአካል እና በሥነ ልቦና ጤናማ የሆኑ ልጆችን ለማሳደግ ወሳኙ አማራጭ ነው።
ሆኖም በተለያየ ምክንያት ልጃቸውን (ልጆቻቸውን) ብቻቸውን ለማሳደግ የተገደዱ እናቶች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመፍታት ጤናማ ዜጋ ማፍራት ይጠበቅባቸዋል።
የሥነ ልቦና ባለሙያው እነዚህ ላጤ እናቶች የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ጥቂት ምክሮች ሰንዝረዋል።
- ጤናማ ስሜት እና ጤናማ አካል እንዳላቸው ማረጋጋጥ፣
- ከውስጥ ግጭት ነፃ መሆን፤ ፍርሃት ካላቸው ለልጆቻቸው እንዳያስተላልፉ መጠንቀቅ
- ከልጆች ጋር ደረጃ በደረጃ፤ እንደ ዕድሜያቸው ሁኔታ ያለውን ሁኔታ በግልፅ ማሳየት እንዲሁም
- ልጆች ከአባታቸው ጋር ግንኙነት ሊያስፈልግ እንደሚችል በማመን ከአባታቸው ጋር እንዲገናኙ ዕድል ማመቻቸት የእነርሱንም ሆነ የልጆቻቸውን ሕይወት በተወሰነ መልኩም ቢሆን ቀላል ያደርገዋል።
ብዙ ጊዜ ፈልገው እና ፈቅደው ላጤ እናቶች የሚሆኑት በኢኮኖሚ፣ በአስተሳሰብ እና በትምህርት የተሻሉ እንደሆኑ ይነገራል። ይህንንኑ ጥያቄ ለሴቶች መብት ተሟጋቿ አክሊል አንስተን ነበር።
"ለብቃት (Empowerment) ሰፊ ትርጓሜ በመኖሩ እነዚህ ሴቶች ብቁ ናቸው ወይም አይደሉም ማለት አልችልም" ብላለች።
ይሁን እንጂ ሰዎች የሚወስኑበት መንገድ ቢለያይም 'ልጅ ካልወለድኩ ሴት አይደለሁም፤ ስለዚህ ጊዜዬ ሳያልፍ ልጅ መውለድ አለብኝ' የምትል ሴት ብቁ (Empowered) እንደሆነች አላምንም፤ ምርጫ ግን ነው" ስትል አብራርታለች።
ምንም እንኳን ውሳኔው ላይ በምን ምክንያት ተደረሰ የሚለው ወሳኝ ቢሆንም የአንድ ሰው ዋጋው የሚለካው በልጅ መኖር እና አለመኖር አይደለም። በመሆኑም ሴትነቷ የሚለካው ልጅ በመውለድ አቅም እና ላጤ እናት በመሆን አይደለም ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
አስገዳጅ ምክንያቶች ከሌሉ በስተቀር ልጆችን የእናት እና የአባት ፍቅር በሚያገኙበት እና ሚናቸውን በሚያዩበት ጤናማ ትዳር ውስጥ ማሳደግ ጥሩ ዜጋ ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን የሥነ ልቦና እና የማኅበራዊ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
_________
ማስታወሻ፡ ይህ ጽሑፍ ከዚህ በፊት የቀረበ ሲሆን፣ አሁን ከጥቂት ማሻሻያ ጋር በድጋሚ የቀረበ ነው።















