ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለፈው ሳምንት በሁለት ክሶች ነጻ የተባሉት አቶ ታዬ ደንደአ ሦስት አዲስ ክሶች ቀረቡባቸው
የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ታዬ ደንደአ ሦስት አዲስ ክሶች ቀረቡባቸው።
ጠበቃቸው አቶ አበራ ንጉሥ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አቶ ታዬ ዛሬ ሰኞ ኅዳር 15/2018 ዓ.ም. ሦስት አዲስ ክሶች ደርሰዋቸዋል።
አቶ ታዬ በዐቃቤ ሕግ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች ፍርድ ቤት በሁለቱ በነጻ ሲያሰናብታቸው በአንዱ ግን ጥፋተኛ ማለቱ ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት ኅዳር 3/2018 ዓ. ም. የአቶ ታዬን ጉዳይ የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና በሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት፤ ከቀረቡለት ሦስት ክሶች የጦር መሣሪያ ሕግን በመተላለፍ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በዚህ ክስ ላይ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመስማት ለዛሬ ኅዳር 15/2018 ዓ. ም. ቀጠሮ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ተጨማሪ ሦስት አዲስ ክሶች መቅረባቸውን አቶ አበራ አስረድተዋል።
ጠበቃው እንደተናገሩት፤ አንደኛው ክስ "ከዚህ ቀደም ከቀረበባቸው ጋር ተመሳሳይነት ያለው" ሲሆን፤ ክሱም "ሁከት እና ብጥብጥ ማስነሳት እንዲሁም በሕግ የተመረጠ መንግሥትን በኃይል ለመናድ መሞከር" የሚል ነው።
ሁለተኛው ክስ በመከላከያ ሠራዊት ላይ "ሐሰተኛ እና የሚያደናግር መረጃ ነዝተዋል" የሚል፤ ሦስተኛው ደግሞ "አገርን የመድፈር ወንጀል" እንደሆነም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም፤ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነው የአገርን፣ የመንግሥትን እና የሕዝብን ደኅንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257 ንዑስ አንቀጽ (ሠ) ተላልፈዋል በሚል የተከሰሱ ሲሆን፤ ዛሬ የቀረበባቸው አዲስ ክስም ከዚህ ጋር እንደሚመሳሰል አቶ አበራ ተናግረዋል።
"ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመመሳጠር መንግሥትን ለመጣል ስውር መሰናዶ ማድረግ፤ ሕዝብን የሚያነሳሳ፣ የሕዝብን ሞራል ዝቅ የሚያደርግ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት መንግሥትን በኃይል ለመናድ መሞከር የሚለው ክስ ባለፈው ከቀረበባቸው ክስ ጋር በፍሬ ነገር ተመሳሳይ ነው" ብለዋል።
አቶ ታዬ የቀረቡባቸው አዲስ ክሶች 'ሆርን ኮንቨርሴሽን' ከተባለ የማኅበራዊ ሚዲያ መደረክ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ጠበቃው ገልጸዋል።
በሦስት ክፍል የተላለፈው ቃለ ምልልስ አቶ ታዬ በእስር ላይ ሳሉ አየር ላይ የዋለ ነው።
"የቀረበው ክስ ዘርዘር ብሎ ሲታይ፤ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ቀርበው ሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰውን ጥቃት እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ አሳሳች እና ሐሰተኛ መረጃ ሰጥተዋል የሚል ነው። ሁለተኛው ክስ፤ በተለይ 'ሆርን ኮንቨርሴሽን' በሚባል ቻናል ላይ አሳሳች መረጃ ሰጥተዋል የሚል ነው።"
ሦስተኛው ክስም 'ሆርን ኮንቨርሴሸን' ከተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ "ባስተላለፉት መረጃ፤ በሕግ የተመረጠው መንግሥት ላይ ዘመቻ በማድረግ የአገሪቱ መንግሥት ላይ የመድፈር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው" በማለት ጠበቃው አብራርተዋል።
አቶ ታዬ ባለፈው ሳምንት ነጻ የተባሉባቸው ክሶች "ከጠላት ጋር ማበር" አና የአገር መከላከያ ሠራዊትን ለመምታት "ዝግጅት አድርገዋል" የሚሉት ሁለት ክሶች ነበሩ።
ባለፈው ሳምንት በፍርድ ቤት ነጻ የተባሉባቸው ክሶች ከዚህ ቀደምም በፍርድ ቤት ታይተው ውድቅ ተደርገው የነበረ ቢሆንም፣ በድጋሚ እንዲታዩ መወሰኑ አይዘነጋም።
አቶ አበራ እንደተናገሩት፤ በዛሬው የችሎት ውሎ 14 ነጥቦች ያሉት የቅጣት ማቅለያ አቅርበዋል።
ከእነዚህ መካከልም አቶ ታዬ ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌላቸው መሆናቸው እና ቤተሰብ አስተዳዳሪነታቸውን ጠቅሰዋል።
"በእስር ላይ ሳሉ አራት ወር ያህል ጨለማ ክፍል በመታሰራቸው ዐይናቸው ላይ የጤና ችግር እንደገጠማቸው" በመጥቀስም የቅጣት ማቅለያቸውን አቅርበዋል።
በተጨማሪም ከመታሰራቸው በፊት ያደረጉት "የልማት ተሳትፎ እና ለበጎ አድራጎት ድርጅት የነበራቸው አስተዋጽኦ" እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እያሉ "ለሕግ የበላይነት እና የፀረ ሙስና ትግል የነበራቸው አስተዋጽኦ" ተካተዋል።
ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ "የጦር መሣርያ ይዘው የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው" እንደነበር ጠቅሶ "ሕግን ከማክበር አንጻር አርአያ መሆን ሲገባቸው ያንን ተላልፈው የፈጸሙት ስለሆነ ቅጣቱ እንዲከብድ" ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመስማት ለኅዳር 23/2018 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምና 2017 ዓ.ም. ሐምሌ ላይ አቶ ታዬ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ሁለቱን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ አሰናብቷቸው እንደነበር ይታወሳል።
ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ጋር በተያያዘ የቀረቡባቸውን ክሶች ደግሞ ከእስር ቤት በዋስ ወጥተው እንዲከላከሉ ተወስኖላቸው የነበረ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ አቶ ታዬ ነጻ የተባሉባቸውን ክሶች በመቃወም ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ የዋስትና መብታቸው ተነስቶ ለእስር ተዳርገዋል።
አቶ ታዬ በአገሪቱ ስላለው የሰላም ሁኔታ እና በመንግሥት ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች ለመገናኛ ብዙኃን በመናገር እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሐሳባቸውን በመግለጽ የሚታወቁ ሲሆን፤ ከሥልጣን የተሰናበቱት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈ ሁለት መስመር ደብዳቤ መሆኑ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ጠንከር ያለ ትችት እና ክስ በሰነዘሩበት ምሽት በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተወስደው አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ቆይተው በፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስ ቢለቀቁም ከግንቦት 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በድጋሚ ታስረዋል።