የዘረ መል ምህንድስና ተደርጎላት ከተወለደች አንድ ዓመት የሞላት በግ

የፎቶው ባለመብት, Abid Bhat/BBC
'ታርሚም' የዘረ መል ምህንድስና የተደረገላት በግ ናት። የተወለደችው በሕንድ ካሽሚር ግዛት ሲሆን፤ አንደኛ ዓመቷን አክብራለች።
'ታርሚም' በአረብኛ አርትኦት ማለት ነው። በሕንድ የመጀመሪያው የዘረ መል ምህንድስና የተደረገላት በግ ስትሆን በሸር ካሽሚር የግብርና ዩኒቨርስቲ እየኖረች ነው።
በዩኒቨርስቲው የሚሠሩ ተመራማሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ታርሚምን ደካማ የሚያደርጋት እና ለበሽታ የሚያጋልጣት የዘረ መሏ ክፍል ተቆርጦ ሕክምና ተደርጎላታል።
መንታ እህቷ ግን የዘረ መል ምህንድስና አልተደረገላትም።
ዶ/ር ሱሀሊ ማግሪ እንዳሉት፤ ነፍሰ ጡር ከሆነች በግ ውስጥ በማደግ ላይ ያለ ጽንስ ላይ ነው ምርምሩ የተጀመረው።
ከጽንሱ ላይ 'myostatin gene' የተባለ የዘረ መል ዓይነት ተወስዶ ምህንድስና ተደርጎለታል። ይህ ዘረ መል የጡንቻ እድገት ላይ ጫና የሚያሳድር ነው።
ከወንድ በግ ዘር ፍሬ ጋር የተዋሀደው የሴት በግ እንቁላል ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት በቤተ ሙከራ እንዲቀመጥ ይደረጋል። ወደ ሴቷ በግ ማሕጸን ውስጥም ይከተታል።
ከ150 ቀናት በኋላ ሁለት የበግ ግልገሎች ተወልደዋል።
"የጎችን ጡንቻ ጠንካራ ማድረግ ነበር ግባችን። ለዚህ መሰናክል የሚሆነው ማዮስታቲን ዘረ መልን በተሳካ ሁኔታ አስወግደናል" ሲሉ ተመራማሪው ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Abid Bhat/BBC
ታርሚም "በጥሩ ሁኔታ እያደገች" እንደሆነ የዩኒቨርስቲው የእንሰሳት ሕክምና ክፍል ዲን ፕ/ር ሪዝ ሻህ ተናግረዋል።
"የሰውነቷ እድገት ጤናማ ነው። ጡንቻዋም በአበረታች ሁኔታ እየጎለበተ ነው" ብለዋል።
የዘረ መል ምህንድስና ካልተደረገላት መንታ እህቷ ጋር ስትነጻጸር ታርሚም የተሻለ ጡንቻ አላት። ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የታርሚም ጡንቻ 10% የላቀ ነው።
ዕድሜዋ እየጨመረ ሲሄድ ጡንቻዋ የበለጠ እየጠነከረ ይሄዳል።
ለዓሥርት ዓመታት ያህል በጎች ላይ የዘረ መል ምርምር ተካሂዷል።
እአአ በ1990ዎቹ በዩናይትድ ኪንግደም 'ትሬሲ' የተባለች በግ በፕሮቲን የበለጸገ ወተት እንድታመርት ተደርጓል።
CRISPR የተባለው የዘረ መል ሕክምና ከጡንቻ ጥንካሬ እንዲሁም በሽታ ከመቋቋም አቅም ጋር ለተያያዙ ሕመሞች መፍትሔ ይሰጣል። ከወሊድ ጋር የተያያዘ ሕክምና የሚደረግበትም መንገድ ነው።
በሕንድ የዘረ መል ምህንድስና የተደረገላትን የመጀመሪያ በግ ለመፍጠር ስምንት አባላት ያሉት የምርምር ቡድን ለሰባት ዓመታት ሠርቷል።
አይቪኤፍ በመጠቀም ጥናት ያደረጉ ሲሆን ሁለት ጊዜ ውርጃ ገጥሟቸዋል።
"ከዜሮ ብንጀምርም ከዚህ በኋላ የምንመራበት ስታንዳርድ አግኝተናል። ለወደፊትም የበለጠ ስኬታማ እንሆናለን" ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያብራራሉ።
ጥናታቸው በካሽሚር ግዛት ያለው የበግ ምርት እንዲጨምር እንደሚረዳ ያምናሉ።
በካሽሚር 60,000 ቶን በግ በዓመት ጥቅም ላይ ቢውልም የሚመረተው ከዚህ ግማሹ ብቻ ነው።
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ የሕዝብ ቁጥር ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ የግጦሽ መሬት እየጠበበ ከመምጣቱ ባሻገር የውሃ አቅርቦትም ውስን ነው።
"በእኛ ግዛት ውስጥ የበግ ግልገል እጥረት አለ። የዘረ መል ምህንድስና የሚደረግላቸው በጎች ክብደታቸው 30% ስለሚጨምር የምግብር አቅርቦትን ዘላቂነት ማረጋገጥ እንችላለን።"
በሕንድ በዓሳማ፣ በፍየል እና ሌሎች እንሰሳት ላይም የዘረ መል ምርምር ይደረጋል።
እአአ በ2012 የተጀመረው የዘረ መል ምህንድስና የሕክምናውን ዘርፍ አዘምኗል።
አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ እና ጃፓን የዘረ መል ምህንድስና የተደረላቸው እንሰሳት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይፈቅዳሉ።
አሜሪካ እና ቻይና በሽታ የሚቋቋሙ ሰብሎችን ለማምረት የዘረ መል ምህንድስና ላይ ጥናት ቀጥለዋል።















