ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሙሽሮች በስጦታ የተሰጠን 40,000 ዶላር ከሠርግ አዳራሽ የሰረቀ ግለሰብ በእስራት ተቀጣ
በሲንጋፖር ከአዲስ ሙሽሮች 40,000 ዶላር የሰረቀው ግለሰብ የጥንዶቹ ደስታ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሶበታል።
ለጥንዶቹ በሰርጋቸው ዕለት በቀይ ፖስታ ተደርጎ የተበረከተላቸውን 39,083 ዶላር የዘረፈው ግለሰብ ደስታቸውን በድንጋጤ ቀይሮታል።
ሊ ዪ ዌይ የተባለ ግለሰብ የሰረቀውን ገንዘብ በቁማር ያጠፋው ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት የአንድ ዓመት እስር እንዲሁም ጥንዶቹን እንዲክስ ተፈርዶበታል።
ለጥንዶቹ ገንዘባቸውን መመለስ ካልቻለ ግን የእስር ጊዜው በ100 ቀናት እንደሚራዘም ጉዳዩን ያየው ችሎት ተገልጿል።
የ36 ዓመቱ ወንጀለኛ ሠርጉ በተካሄደበት ሆቴል ውስጥ በአስተናጋጅነት ይሰራ ነበር የተባለ ሲሆን ገንዘቡ የት እንደሚቀመጥ አስቀድሞ ያውቅ ነበር ሲል ዐቃቤ ሕግ ተናግሯል።
በበርካታ እስያውን ባሕል መሰረት በሠርግ ላይ እንዲታደሙ የሚጠሩ እንግዶች ለሙሽሮቹ በቀይ ፖስታ ውስጥ ገንዘብ በመክተት ስጦታ ያበረክታሉ፤ ይህም እንደ መልካም እድል ምኞት ይቆጠራል።
እነዚህ ፖስታዎች ብዙ ጊዜ የሚቀመጡት በሠርጉ አዳራሽ ተለይቶ በሚገኝ ትልቅ ሳጥን ውስጥ ሲሆን እድምተኞቹ ወደ አዳራሹ ከመግባታቸው በፊት በዚያ እያለፉ ስጦታቸውን ያስቀምጣሉ።
በሚያዝያ ወር ላይ በተካሄደው ሠርግ ላይ ያልተጋበዘው ሊ በአዳራሹ ውስጥ የተቀመጡትን ሁለት ሳጥኖች ጠባቂ አለመኖሩን ሲያይ ዘርፏቸዋል።
የሠርጉ ደጋሾች የሳጥኖቹን መጥፋት እንዳስተዋሉ ለፖሊስ አመልክተዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ሊ የተወሰኑ ዶላሮችን ልብስ ለመግዛት እንዲሁም ለቁማር በአራት ሰዓታት ውስጥ ማጥፋቱን ገልጿል።
ከዚያ በኋላ የሰረቀውን አብዛኛው ገንዘብ በሦስት ቀናት ውስጥ በኦንላየን ቁመራ ላይ ማዋሉ ታውቋል።
ከጥቂት ቀናት በኋላ በቁጥጥር ስር ሲውል ፖሊስ በእግዚብትነት መያዝ የቻለው 3000 የሲንጋፖር ዶላር ብቻ ነበር።
በሲንጋፖር በቀይ ፖስታ ውስጥ ገንዘብ ጨምሮ ለአዲስ ተጋቢዎች መስጠት እየተለመደ መጥቷል።
አንዳንዶች ለአዲሶቹ ሙሽሮች የሰርግ ወጪያቸውን እንደ መሸፈን አድርገው ይቆጥሩታል።
በየዓመቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚካሄዱ ሠርጎች ምን ያህል ገንዘብ በስጦታ መልክ መስጠት እንደሚኖርባቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች በኦንላይን ይለቀቃሉ።
በበርካታ የእስያ አገራት ባሕል መሠረት ቀይ ፖስታ ለሕጻናት ወይንም ላላገቡ ታዳጊዎች በአዲስ ዓመት ወቅት ይሰጣል።