በጣሊያን 200 የማፊያ ቡድን አባላት 2 ሺህ 200 ዓመት ተፈረደባቸው

ዳኞች

የፎቶው ባለመብት, AP

በጣሊያን ከ200 በላይ የሚሆኑ የማፊያ ቡድን አባላት በድምሩ የ2 ሺህ 200 ዓመት እስራት ተበይኖባቸዋል።

ከማፊያ ቡድን ጋር በተያያዘም ትልቁ ችሎትም እንደሆነ ተጠቅሷል።

‘ንድራንጌታ’ በጣልያን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው አውሮፓ ‘አደገኛው’ የማፊያ ቡድን ነው። መረቡ ደግሞ ከደቡብ አሜሪካ እስከ አውስትራሊያ የተዘረጋ ነው።

ታዲያ ሶስት ዓመታትን የፈጀው የፍርድ ሂደት ከዚህ የማፊያ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው ተከሳሾችን ከከባድ ዘረፍና የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋር በተገናኘ ፈጽመውታል የተባለውን ወንጀል ሲመለከት ቆይቷል።

ፍርዱ ከተላለፈባቸው ሰዎች መካከል የቀድሞ የጣሊያን ምክር ቤት አባል ይገኙበታል። እሳቸው ተሳትፏቸውን ክደው ይግባኝ ጠይቀዋል።

‘ንድራንጌታ’ በአውሮፓ ከሚገኙ አደገኛ የማፊያ ቡድኖች አንዱ ነው።

ቡድኑ በተለይም በደቡብ ጣልያን ፖለቲካዊና ማህበረዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው።

በክሱ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች እና ፖለቲከኞች መሳተፋቸው በጣልያን የመንግስት ተቋማት ውስጥ ማፊያዎች ምን ያህል ዘልቀው እንደገቡ የሚያመላክት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፍርዱ ከተላለፈባቸው ሰዎች መካከል የሕግ ባለሙያ የሆኑት የቀድሞ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ ፓርቲና የጣልያን ምክር ቤት አባል የነበሩት ጊንካርሎ ፒቲሊ ይገኙበታል።

ፒቲሊ ከማፊያ ቡድን አባላት ጋር ትስስር በመፍጠራቸው የ11 ዓመት እስራት ተበይኖባቸዋል።

በተጨማሪም የመንግሥት ሰራተኞችና ከፍተኛ ባለስልጣናት እና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎች ፍርዱ ከተላለፈባቸው ሰዎች መካከል ሲሆኑ ‘ንድራንጌታ’ ህገ ወጥ ተግባሩን በህጋዊ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲያንቀሳቀስና የመንግስት ተቋማት ውስጥ ዘልቆ እንዲገባ ረድተውታል።

በዚህ ሂደት ከ100 በላይ ተከሳሾች ክሳቸው ተቋርጧል።

ጉዳዩን እየተከታተሉ የሚገኙ ዳኞች ለደህንነታቸው በመስጋታቸው በከፍተኛ የፖሊስ ጥበቃ ስር ይገኛሉ።

በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ከሆነችውና ካላብሪያ ከተባለችው አከባቢ የተወለደው ‘ንድራንጌታ’ በዓለም ላይ ከሚገኙ እጅግ አደገኛ የማፊያ ቡድኖች አንዱ እንደሆነ ይታመናል። ቡድኑ በአውሮፓ 80 በመቶ የሚሆነውን የኮኬይን ንግድ እንደተቆጣጠረም ይታመናል።

ይህ የማፊያ ቡድን በዓመት እስከ 60 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ያገኛል።

የወንጀለኞቹን የፍርድ ሂደት ሲከታተል የቆየው ችሎት ላሜዚያ ከተሰኘችው የጣልያን ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ የሚገኝ ነው። ችሎቱ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት ሲሆን፣ ተከሳሾቹን በታጠረ ብረት ውስጥ ማቆየት ይችላል። በተጨማሪም 600 ጠበቆችን እና 900 ምስክሮችን የመያዝ አቅም አለው።

ተከሳሾቹ በግድያ፣ በከባድ ዝርፊያ፣ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር፣ በአራጣ በማበደር፣ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቅምና ህገ ወጥ ገንዘብን ህጋዊ በማስመሰል ነው የተከሰሱት።

ይህ ይህ የማፊያ ቡድን አህጉራትን አቋርጦ በደቡብ አሜሪካና አውስትራሊያ ጭምር የነበረው የወንጀል ተግባር በሶስት ዓመት የፍርድ ሂደት ውስጥ ተጋልጧል።

የቡድኑ አባላት በዝቅተኛው የአከባቢ መዋቅር ኢኮኖሚና በመንግሥት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በጤና ስርዓቱ ጭምር ዘልቀው በመግባት ጨረታዎችን አጭበርብረዋል። ለመንግሥት ኃላፊዎች ጉቦ ሰጥተዋል።

ከአውሮፓውያኑ 1980 ወዲህ በዓይነቱ ትልቅ በተባለው በዚህ የፍርድ ሂደት ዳኞች የምስክሮችን ቃል ለመስማት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዓታትን ፈጅተዋል።

የቀድሞ የማፊያ ቡድኑ አባል በፍርድ ሂደቱ ተባባሪ ሆኖ መረጃዎችን ሰጥቷል። በዚህ መረጃዎች በማፊያ ቡድኑ ውስጥ ቁልፍ ስፍራ ያላቸውን የማንኮስ ቤተሰብና ተባባሪዎቹን አጋልጧል።

ያማንኮስ ቤተሰብ መነሻው ሊምባዲ ከተሰኘ አነስተኛ ከተማ ሲሆን የ‘ንድራንጌታ’ ከመሰረቱት 150 አደገኛ ማፊያዎች አንዱ ነው።

አብዛኞቹ ተከሳሾች በአውሮፓውያኑ ታህሳስ ወር 2019 በጣልያን በ11 ክልሎች የተጀመረውን ሰፊ ምርመራ ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው። ይህ ምርመራ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2016 ነው።

በዚህ ጊዜ ‘ንድራንጌታ የተቆጣጠረውን ቪቦ ቫሌንታ የተሰኘ ቦታ ላይ ወንጀለኞችን ለመያዝ 2 ሺህ 500 ፖሊሶች ተሰማርተዋል።

ከ50 በላይ የማፊያ ቡድኑ አባላት ከችሎቱ ጋር ለመተባበር ተስማምተዋል። የነሱም የምስክርነት ቃል የማፊያ ቡድኑን የተደበቀ ስራ አደባባይ አስጥቶታል።

ችሎቱ የ‘ንድራንጌታ’ የማፊያ ቡድን አባላት በመቃብር ስፍራዎች መሳሪያ እንደደበቁ፣ አደንዛዥ ዕጽ ለማዘዋወር አምቡላንስ እንደተጠቀሙ እና ማሪዋና የተሰኘውን ዕጽ ለማብቀል የመንግሥትን ውሃ እንደተጠቀሙ ሰምቷል።

ይህንን የማፊያ ቡድኑን አባላት የተቃወሙ ወይም ለመተባበር አሻፈረኝ ያሉ ሰዎች ከባድ ቅጣት ተቀበለዋል። ይህም በቤታቸው ደጃፍ ላይ የውሻ ቡችሎችንና የፍየል ጭንቀላትን በማስቀመጥ ማስፈራራት፣ ተሽከርካሪያቸው ላይ ጥቃት ማድረስ እና ሱቆቻቸውን ማውደም ይጨምራል።

አንቶኒዮ ኒካሶ የተባሉ የተደራጁ ወንጀሎች ላይ ክትትል የሚያደርጉና የሚጽፉ ባለሙያ ስለፍርዱ ሲናገሩ “ ንድራንጌታ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ፋይናንስ ጉዳዮች ባለው የጠለቀ ግንኙነት ምክንያት ቡድኑን መጋፈጥ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ የመጀመሪያ የፍርድ ሂደቱ አመላክቷል” ብለዋል።