ብልጽግና "ከ8 ሺህ በላይ" አመራሮች ላይ እርምጃ ሲወስድ፣ ክልሎች የአመራር ለውጥ እና ሽግሽግ አደረጉ

ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ

የፎቶው ባለመብት, Prosperity Party

የምስሉ መግለጫ, ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ

ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በመላው አገሪቱ ካሉት አባላቱ መካከል ወደ ዘጠኝ ሺህ በሚጠጉት ላይ በሥነ ምግባር ጉድለት እና በአፈጻጸም ድክመት ምክንያት እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ይህንን ያሉት በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የተሰጡ ውሳኔዎችን አስመልክተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

አቶ አደም ላለፉት ሦስት ወራት የፓርቲውን ተቋማዊ አቅም የሚያጠናክሩ የውስጠ ፓርቲ ሥራዎችን መሠራታቸውን ተናግረው፣ በተደረገው ውይይት እና ግምገማ "እውቅና ለሚገባቸው እውቅና መሰጠቱን ደከም ያሉት ላይ ደግሞ ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ" መወሰዱን ተናግረዋል።

"በተለይ የእርምት እርምጃ ከመውሰድ አኳያ በአጠቃላይ 8,613 በሚሆኑ አመራሮች ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ ተወስዷል።"

የተወሰደውንም እርምጃ ሲያብራሩም አባላቱን ከኃላፊነት ከማንሳት ጀምሮ ሽግሽግ እስከማድረግ የሚደርስ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብልጽግና ፓርቲ ካደረገው የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በኋላ በሺዎች በሚቆጠሩ አባላቱ ላይ እርምጃ መውሰዱ ከተገለጸ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ ክልልሎች አመራሮች ላይ ለውጦች እየታዩ ነው።

ባለፉት ቀናት ከፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ጋር በተያያዘ በሚመስል ሁኔታ የተለያዩ ክልሎች ኃላፊዎቻቸውን በማንሳት በአዲስ የመተካት፣ ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የማዘዋወር እንዲሁም የማሸጋሸግ እርምጃዎች መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልልር የቀደሙ የክልል ኃላፊዎችን በማንሳት በአዲስ ሲተካ የተወሰኑት፣ ደግሞ ወደ ተለያዩ ቢሮዎች ተዛውረው እንዲሠሩ መደረጉን ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ አቶ አረጋ ከበደ አዲሶቹ ተሿሚዎች ኃላፊነቱ የተሰጣቸው የአመራር ብቃት፣ የሥራ ልምድ፣ የትምህርት ዝግጅት እና ሥነ ምግባራቸው መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከሾሟቸው 35 አዳዲስ ተሿሚዎች መካከል ሰባቱ አማካሪዎቻቸው መሆናቸው በክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ገጽ ላይ ወጣው መረጃ ያሳያል።

የደቡብ ምዕራብ ክልልም እንዲሁ "በብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሠረት" በማለት በክልሉ ከከፍተኛ አመራሮች እስከ ታችኛው መዋቅር ያሉት አመራሮች የግምገማና የምዘና መድረክ መካሄዱን ጠቅሷል።

በዚህም በክልል ደረጃ አመራሩን መልሶ የማደራጀት ሥራ መከናወኑን የገለጸው ክልሉ፣ አዲስ አመራሮችን መሾሙን እና ማሸጋሸጉን አስታውቋል።

ይህም የተከናወነው የአመራር ምደባው የአመራርን ውጤታማነት፣ ሥነ ምግባርን እና ዝግጁነትን መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቁሟል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ የተሾሙ እና የተሸጋሸጉ አመራሮች ቁጥር 15 ነው።

የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉ በ2017 በተደረገው አመራር ምዘና መሠረት "የክልሉን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል' እንደሚችሉ የታመነባቸው በማለት ለ66 አመራሮች ሹመት እና ሽግሽግ መደረጉን አስታውቋል።

የአመራር ለውጥ እና ሽግሽግ ከተካሄደባቸው ክልሎች መካከል አንዱ የሆነው ደቡብ ኢትዮጵያም እንዲሁ ከጥቅምት 10/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለውጥ ማድረጉን ገልጿል።

በዚህም በክልሉ ላሉ ለ11 ቢሮዎች አዲስ የአመራር ሹመት እና ሽግሽግ መደረጉን አስታውቆ ከዚህ ውጪ ያሉት ግን ባሉበት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ገልጿል።

ሥነ ምግባር እና የሥራ አፈጻጸም ብቃትን መሠረት በማድረግ ተካሄደ የተባለው ሹመት እና ሽግሽግ ይፋ የሆነው በአገሪቱ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ምርጫ ሰባት ያህል ወራት ሲቀሩት ነው።

የብልጽግና ፓርቲን ሥራ አስፈፋሚ ኮሚቴን ስብሰባ ተከትሎ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የተካሄደው የአመራር ለውጥ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት "በተመደበበት ቦታ በተሰጠው ኃላፊነት ሕዝቡን በቅንነት በታማኝነት የማያገለግል፣ የሥነ ምግባር ችግር ያለበት፣ በብልሹ አሠራር ውስጥ በሌብነት የተዘፈቀ" ላይ እርምጃዎች ይወሰዳሉ።

አክለውም "የተሰጠውን ተግባር በውጤታማነት የማይፈጽም የፓርቲ አመራር፣ ተገልጋይን አክብሮ ሕዝቡን አክብሮ፣ በፓርቲው መርሆች እና እሴቶች እየተመራ የሕዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማይንቀሳቀስ አመራር ላይ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል" ብለዋል።

ባለፉት ቀናት የአመራር ለውጥ እና ሽግሽግ ያደረጉት ክልሎች ውሳኔውን ከማሳወቅ ውጪ የትኞቹ አመራሮች በብቃት ማነስ፣ በሥነ ምግባር ይሁኑ በየትኘው ችግር ከቦታቸው እንደተነሱ የሰጡት ምክንያት የለም።