የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ የዓለም ባንክን የድህነት ምጣኔ ስሌት "ተጨባጭ ሁኔታን ያላማከለ" በማለት ተቹ

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ

የፎቶው ባለመብት, PM Office/FB

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ፤ በአውሮፓውያኑ 2025 በኢትዮጵያ የድህነት ምጣኔ "ወደ 43 በመቶ" ከፍ እንደሚል የሚገልጽ ሪፖርት ያወጣው የዓለም ባንክ የሚጠቀመው የድህነት ስሌት አሠራር "ተጨባጭ ሁኔታን ያላማከለ" እንደሆነ ተናገሩ።

የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም ስሌት "እንደ የትምህርት ቤት ምገባ" ያሉ የመንግሥት ተግባራትን "ከግምት ያላስገባ" እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ የድህነት ቁጥርን በተመለከተ ተቀባይነት ያለው "የመንግሥት ኦፊሻል መረጃ" መሆኑን ገልጸዋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም ይህንን ትችት ያሰሙት የ2018 በጀት ዓመት የ100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ሪፖርትን ባቀረቡበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግምገማ ላይ ነው።

ዶ/ር ፍጹም አብዛኛዎቹ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ያስመገዘቡትን አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ሲነጻጸር ከፍ ያለ እንደሆነ ረቡዕ ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም. በተደረገው ግምገማ ላይ ገልጸዋል።

2.5 ቢሊዮን ዶላር የተገኘበት የወጪ ንግድ አፈጻጸምም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አንጻር በ65 በመቶ የበለጠ መሆኑን አስረድተዋል። ለውጭ ገበያ ከቀረቡት ወርቅ፣ ቡና፣ ኤሌክትሪክ እና የቁም እንስሳት የተገኘው ገቢም ከታቀደው በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

"አካታች የሆነ የጋራ ብልጽግናን ከማሳካት አኳያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ውጤት እያመጡ" መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ "አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌትነት [ለመሆን] በ10 ዓመቱ ዕቅዳችን ላይ ያስቀመጥነውን ግብ ከማሳካት አኳያ ጉዟችን የተሳካ እንደሆነ ማየት ይቻላል" ብለዋል።

"ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ሲመዘገብ ወደ ተጠቃሚነት የመሸጋገር ዕድሉ ሰፊ ነው" ሲሉም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ግን "የተለያዩ ተቋማት የተለያየ ቁጥር" እንደሚያወጡ በገለጻቸው ላይ አንስተዋል።

ዶ/ር ፍጹም እንደሚያስረዱት፤ ከእነዚህ አንዱ "ከድህንነት አኳያ የሚነሳ ቁጥር" ነው። "የተለያዩ ተቋማት" ይህንን ዳታ ለማግኘት "የተለያየ የስሌት ሞዴል" እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት የዓለም ባንክ የድህነት ወለልን ለማስላት የሚጠቀምበትን 'በቀን የሦስት ዶላር ገቢ' አሠራርን ነው።

"ለምሳሌ poverty line (የድህነት ወለል) የምንለው ቁጥር አለ። poverty line ሦስት ዶላር በቀን የሚል ነው፤ በቅርብ የዓለም ባንክ አሻሽሎ እየተጠቀመ ያለው። በቀን 450 ብር ማለት ነው። ይህ ማለት በቀን 450 ብር የማያገኝ ሰው ደሃ ነው ብሎ [ይቆጥራል ማለት] ነው" ሲሉ አሠራሩ አለበት ያሉትን ጉድለት አንስተዋል።

የዓለም ባንክ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ባወጣው የኢትዮጵያ "የድህነት እና ፍትሐዊነት መግለጫ" ላይ የድህነት ምጣኔን ለመለካት የተጠቀመው ይህንን መለኪያ ነበር።

የተቋሙ መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "ድህነትን ለመቀነስ ለሁለት አስርት ዓመታት" ያከናወናቸው ተግባራት ያስገኙት ውጤት ወደ ኋላ መመለሱን የሚያመለክት ነው።

የስንዴ መሸጫ ላይ ብር የምትቆጥር ሴት እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከደህንነት ወለል በታች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2016 ከነበረበት "33 በመቶ" በ2019 "ወደ 39 በመቶ ከፍ" ማለቱን የተቋሙ መግለጫ ያስረዳል። ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት በቀሩት የአውሮፓውያኑ 2025 ደግሞ ይህ ቁጥር "ወደ 43 በመቶ ከፍ ይላል" ተብሎ እንደሚጠበቅ አስፍሯል።

የኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳ ያስመዘገበችው ውጤት ወደ ኋላ ለመመለሱ በምክንያትነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል "የኮቪድ 19 ወረርሽኝ"፣ "የትግራይ ጦርነት" እና "የከፋ ድርቅ" ይገኙበታል። "የጠቅላላ አገራዊ ምርት ዕድገት መቀዛቀዝ" እና "የዋጋ ግሽበት መጨመርም" በምክንያትነት ተነስተዋል።

"የዋጋ ግሽበቱ በከተሞች የሚኖሩ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ" ማሳደሩን የሚገልጸው የዓለም ባንክ መግለጫ፤ በገጠር የሚገኙ ቤተሰቦችም ቢሆኑ "በገበያ ተሳትፎ ውስንነት ምክንያት ከምግብ ዋጋዎች መጨመር ተጠቃሚ" መሆን እንዳልቻሉ ያብራሯል።

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም፤ የድህነት ምጣኔው በ2026 "ቀስ በቀስ ይቀንሳል" ብሎ እንደሚጠብቅ አስታውቋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም ግን የዚህ ዓይነቱን ሪፖርቶች መረጃ ለማጠናቀር ጥቅም ላይ የሚውለው የዓለም ባንክ መለኪያ፤ በአገራት ውስጥ ያለውን "ነባራዊ ሁኔታ ያላማከለ" መሆኑን በማንሳት ተችዋል።

በተለያዩ አገራት መካከል ያለውን የኑሮ ወጪ እና የዋጋ ደረጃ ልዩነት (purchasing power parity) ግምት ውስጥ መግባት ያለበት አንድ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

"እንደ አገር የምንሠራቸው በዚያ ዓይነት ሞዴሎች ላይ የማይታዩ ድህነትን የሚቀርፉ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ። ከትምህርት ቤት ምገባ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች አሉን" ብለዋል። የዓለም ባንክ የሚከተለው ሞዴል መንግሥት የሚወስዳቸውን እነዚህን እርምጃዎች "ከግምት አያስገባም" በማለት ተችተዋል።

"እንዲህ ዓይነት ተጨባጭ ሁኔታውን (context) ያላማከለ አጠቃላይ የዓለም አገራትን በአንድ ቅርጫት ውስጥ የሚጨፈልቅ ዓይነት አሠራር ተሂዶ የሚመጡ ቁጥሮች አሉ" ሲሉም ተደምጠዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የግምገማ መድረክ

የፎቶው ባለመብት, PM Office/FB

የምስሉ መግለጫ, የሚኒስትሮች ምክር ቤት የግምገማ መድረክ

የአገሪቱ የግብርና ምርት ከ2010 ዓ.ም. ጋር ሲነጻጸር "በአምስት እጥፍ" ወይም "በ430 ፐርሰንት" መጨመሩን የጠቀሱት ዶ/ር ፍጹም፤ በዚህ ደረጃ ካደገው ምርት ውስጥ "90 ፐርሰንት በላዩ የሚመጣው ከአነስተኛ አርሶ አደር" መሆኑን አስረድተዋል።

"[የ]አርሶ አደሩ ምርት በአምስት እጥፍ ካደገ፣ ከ400 ፐርሰንት በላይ ካደገ እያንዳንዱ አርሶ አደር ቤት የገባ ገቢ አለ ማለት ነው። ይሄ ገቢ የአርሶ አደሩን ኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል" ሲሉ አብራርተዋል።

"በየቦታው" በሚጓዙባቸው ጊዜያትም የአርሶ አደሩ የማውጣት አቅም "መሻሻሉን" እንደሚመለከቱም አንስተዋል። አርሶ አደሮች "ፓምፕም በመግዛትም ይሁን ሌሎች የግብርና ማሽነሪዎቹን በመግዛት የሚያደርጓቸው ኢንቨስትመንቶች ተሻሽሏል" ብለዋል።

መንግሥት ሁለት ጊዜ "በእያንዳንዱ ሰው በቀን ሲሰላ የዓለም ባንክ የድህነት ወለል ያለውን የሚያክል የደመወዝ ጭማሪ" ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት "ፈጠራ የታከለባቸው አማራጮችን" በመጠቀም "የትምህርት ቤት ምገባ" እና "ማኅበራዊ አገልግሎቶችን" እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

"የአቅመ ደካማ ቤቶች የማደስ" እንዲሁም የገጠር እና የከተማ ኮሪደር ፕሮጀክቶች ያስገኟቸው "ትሩፋቶች የዜጎችን ሕይወት ከማሻሻል አኳያ ትልቅ ሚና" እንዳላቸው ገልጸዋል።

ዶ/ር ፍጹም እነዚህን የመንግሥት ተግባራት "ከግምት ውስጥ አያስገባም" በማለት የተቹት ይህ አሠራር "ድሮም" የነበረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ አክለውም፤ "ማንኛውም ሉዐላዊ መንግሥት የራሱ ኦፊሻል መረጃ አለው። ያ ኦፊሻል መረጃ ነው ተቀባይነት የሚያገኘው ማለት ነው" ብለዋል።

ከዚህ ጋራ በተያያዘ መንግሥት "የራሱን መረጃ" እያዘጋጀ መሆኑንም አስታውቀዋል። "እኛ ግን የራሳችንን መረጃ፣ የትኛውም የአፍሪካ መንግሥት ኢንቨስት አድርጎ [በማያውቀው] ደረጃ ኢንቨስት አድርገን እያለማን እንገኛለን" ያሉት ዶ/ር ፍጹም፤ "የዚህ መረጃ ውጤት በቅርቡ እንደሚመጣ" ተናግረዋል።