በስደተኞች ጉዳይ በተፈጠረ አለመግባባት የኔዘርላንድስ ጥምር መንግሥት ተበተነ

ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ

የኔዘርላንድስ መንግሥት በስደተኞች ጉዳይ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ቀውስ እንደገጠመው ተገለጸ።

የአገሪቱ ጥምር ፓርቲዎች የጥገኝነት ጠያቂዎችን ፖሊሲ በተመለከተ መግባባት እንዳልቻሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ ተናግረዋል።

ሥልጣን መልቀቂያ ለንጉሥ ዊልያም አሌክሳንደር እንደሚያስገቡም ገልጸዋል።

አራቱ ፓርቲዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ባደረጉት ውይይት መስማማት አልቻሉም።

መንግሥቱ የተመሠረተው ከዓመት ተኩል በፊት ሲሆን ፓርቲዎቹ በስደተኞች ጉዳይ ተስማምተው አያውቁም።

በዚህም ምክንያት በቀጣይ ጥቅምት ምርጫ ሊካሄድ እንደሚችል የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ወግ አጥባቂው የጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ ፓርቲ ቪቪዲ ጥገኝነት ጠያቂዎችን የመገደብ ዕቅድ አለው። ይህም ባለፈው ዓመት የስደተኞች መቆያዎች መጨናነቅን ተከትሎ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ በጥምር ፓርቲው ተቃውሞ ገጥሞታል።

በዚህ ምክንያት የመንግሥት መዋቅሩ ቀውስ እንደገጠመው መሪው አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ተናግረዋል።

ሥልጣን መልቀቂያ ለንጉሥ ዊልያም አሌክሳንደር ዛሬ እንደሚያስገቡም ገልጸዋል።

አዲስ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ሚኒስትሮቻቸው በኃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉም አክለዋል።

የጥገኝነት ማመልከቻ ባለፈው ዓመት በሦስት እጥፍ ጨምሮ 47,000 ደርሷል።

የመንግሥት ኃላፊዎች በዚህ ዓመት ቢያንስ 70,000 ማመልከቻዎች ይገባሉ ብለው እንደጠበቁም ገልጸዋል።

በጦርነት ምክንያት የተሰደዱ ሰዎች ወደ ኔዘርላንድስ ማስገባት የሚችሏቸውን የቤተሰቦች ቁጥር በወር ወደ 200 የሚቀንስ ዕቅድ ለማሳለፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገድደው ነበር።

ሆኖም ግን ክርስቲያን ዩኒየን እና ፕሮ-ፋሚሊ ፓርቲ የተባሉት ፓርቲዎች እንዲሁም ዲ66 የተባለውም ጥምር ፓርቲዎች አልፈቀዱም።

ካቢኔያቸው ሥራ መልቀቁን ለጋዜጠኞች ሲገልጹ “ውሳኔው ከባድ ነበር” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በጥምር ፓርቲዎቹ መካከል ያለው ልዩነት “ሊታረቅ የማይችል” እንደሆነም አክለዋል።

“ሁሉም ፓርቲዎች መፍትሄ ለመፈለግ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ግን በስደተኞች ጉዳይ መስማማት አልቻልንም” ሲሉም አክለዋል።

እንደ አማካይ መንገድ የስደተኞችን ቁጥር መቀነስ ሲያስፈልግ ለመገደብ የቀረበው ሐሳብም አስታራቂ አልሆነም።

የክርስቲያን ዩኒየን ፓርቲ ቃል አቀባይ ቲም ኩጂስተን “አራቱ ፓርቲዎች ሊግባቡ አልቻሉም። ስለዚህ ይህንን መንግሥት ልንበትን ወስነናል” ብለዋል።

የ56 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱን ከ2010 ጀምሮ በመምራት አገሪቱን ለረዥም ጊዜ ያስተዳደሩ መሪ ናቸው።

እንደ ፒቪቪ ያሉ አክራሪ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ከመነሳታቸው ጋር በተያያዘ የስደተኞች ጉዳይን በተመለከተ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ጫና ሲደረግ ቆይቷል።