የአሜሪካ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ከትራምፕ መኖሪያ ቤት ጥብቅ ምስጢራዊ ሰነዶችን ወሰደ

የአሜሪካ የፌደራል ወንጀል ምርመራ (ኤፍ.ቢ.አይ) በፍሎሪዳ በሚገኘው የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤት በተካሄደ ብርበራ ጥብቅ ምስጢራዊ ሰነዶች መውሰዳቸውን የፍተሻ ማዘዣው አመለከተ።

በዚህም የኤፍቢአይ ወኪሎች በአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ አደገኛ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ቲ.ኤስ/ ኤስ.ሲ.አይ በሚል ስያሜ የተለዩ እና ምልክት የተደረገባቸው አስራ አንድ ሰነዶችን መያዝ ችለዋል።

በአሜሪካ ታሪክ በወንጀል ምርመራ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ቤት ብርበራ ሲካሄድ ይህ የትራምፕ ቤት የመጀመሪያው ነው።

የሰነዶቹ ዝርዝር አርብ ለሕዝብ ይፋ የሆነው ዳኛው፣ ማር አ ላጎ የሚገኘውን የትራምፕ መኖሪያ ቤት ለመፈተሽ የሚያስችል የማዘዣ ዝርዝር ያካተተ ባለ ሰባት ገጽ ሰነድ ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

ሰነዱ እንደሚለው የፎቶግራፍ አልበም፣ በእጅ የተጻፈ ማስታወሻ፣ ያልተገለጸ፤ ነገር ግን ስለ "የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት" መረጃ እና የረጅም ጊዜ የትራምፕ አጋር የሆነውን ሮጀር ስቶንን ወክለው የተጻፈ የምህረት ደብዳቤን ጨምሮ ከ20 ሳጥን በላይ ሰኞ ዕለት በወንጀል መርማሪዎቹ ተወስደዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ምስጢራዊ ሰነዶችን የያዙ አራት ፋይሎች የተገኙ ሲሆን፣ በፋይሎቹ ውስጥ ሦስት ምስጢራዊ ሰነዶች እና ምስጢራቸው የተጠበቀ ቁሳቁሶች ተገኝተዋል።

ማዘዣው እንዳመለከተው የኤፍቢአይ ወኪሎች፣ አደገኛ ሊሆኑ የሚችሉ የብሔራዊ ደኅንነት መረጃዎችን መያዝ ወይም ማስተላለፍ ሕገ ወጥ የሚያደርገውን የሕግ ጥሰትን እየተመለከቱ ነው።

በምስጢራዊነታቸው ተለይተው የተቀመጡ ሰነዶች እና ቁሳቁሶችን መውሰድ በሕግ የተከለከለ ነው።

ትራምፕ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜም በዚህ ወንጀል የሚያስቀጣውን ቅጣት ጨምረውታል። ድርጊቱ አሁን ላይ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስር ሊያስቀጣ ይችላል።

የማዘዣው ማስታወሻ እንደሚለው ማር አ ላጎ የተካሄደው ፍተሻ በትራምፕ መኖሪያ ቤት ብቻ የተገደበ አልነበረም። ‘45 ኦፊስ’ እና የሰነዶች ማከማቻ ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን፤ ነገር ግን ትራምፕ እና ባልደረቦቻቸው ይጠቀሙበት የነበረውን የግል የእንግዳ ክፍሎችን አይጨምርም።

የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ጉዳዩ ሐሙስ ዕለት ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ጉዳዩ በምርመራ ላይ ባለበት ወቅት ይፋ እንዲደርግ መጠየቁም ያልተለመደ ነው ተብሏል።

የትራምፕ ጽህፈት ቤት በበኩሉ አርብ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሥልጣን ዘመናቸው፣ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ምስጢራዊ የነበሩ ሰነዶችን ምስጢራዊነታቸው እንዲያበቃ (Declassify) አድርገዋል ብሏል።

“ሰነዶቹን ከቢሯቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው መወሰዳቸው ለዚህ ማሳያ ነው” ሲልም መግለጫው አክሏል።

"ሰነዶቹን የመለየትና የመከፋፈል ሥልጣኑም የፕሬዝዳንቱ ብቻ ነው” ብሏል መግለጫው።

የሕግ ባለሙያዎች ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እነዚህ ክርክሮች በፍርድ ቤት ይቀጥሉ አይቀጥሉ ግልጽ አይደለም ብለዋል።

ቀደም ብሎ በፍትሕ መሥሪያ ቤት ሲያገለግሉ የነበሩት የሕግ ባለሙያ ቶም ዱፕሪ፣ “ፕሬዝዳንቶች ሰነዶችን መለየት ይችላሉ፤ ነገር ግን የአሠራር ሂደቶችን መከተል አለባቸው” ይላሉ።

“ፎርሞችን መሙላት አለባቸው። ፈቃድ መስጠት አለባቸው። ዝም ብሎ እነዚህ ሰነዶች ተለይተዋል ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ሂደቶችን መከተል አለባቸው። ትራምፕ ይህን ስለመከተላቸው ግልጽ አይደለም” ብለዋል።

የትራምፕ ቃል አቀባይ ታይለር ቡዶዊች፣ የጆ ባይደንን አስተዳደር በዋና የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ላይ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማውጣት ይከሳሉ።

የትራምፕ አጋሮችም ትራምፕ በ2024 ምርጫ ለመወዳደር እያሰቡ በመሆናቸው በቤታቸው ላይ የተፈጸመው ፍተሻ ፖለቲካዊ ነው ሲሉ አውግዘውታል።

የሕግ አስፈጻሚ ወኪሎችም የኤፍቢአይ ብርበራን ተከትሎ በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ በኦንላይን የሚደርሰውን ማስፈራሪያ እየተከታተሉ መሆኑ ተገልጿል።

ማዘዣውን በግል ያጸደቀው የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ፣ ሐሙስ ዕለት “ቁርጠኛ እና አገር ወዳድ የሕዝብ አገልጋዮች” ሲሉ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ወኪሎችን ተከላክለዋል።

“ታማኝነታቸው ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ሲጠቃ ዝም ብዬም አልመለከትም” ሲሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።