ልጃቸውን በጋሪ እየገፋች የነበረችው ባለቤቱን በስለት 26 ጊዜ ወግቶ የገደለው ግለሰብ በእድሜ ልክ እስራት ተቀጣ

በዩናይትድ ኪንግደም የሰባት ወር ጨቅላ ልጃቸውን መንገድ ላይ በህጻናት ጋሪ እየገፋች የነበረችውን ባለቤቱን በስለት በተደጋጋሚ ወግቶ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ በእድሜ ልክ እስራት ተቀጣ።

ከዚህ ቀደም ጥቃት ፈጽሞባት የነበረውን ባለቤቷን ፈርታ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥታ በብራድፎርድ የሴቶች መጠለያ መኖሪያዋን አድርጋ የነበረችው የ27 ዓመቷ ኩሉሱማ አክተር በልጇ ፊት የተገደለችው 26 ጊዜ በባለቤቷ በስለት ተወግታ ነው።

ኩሉሱማ ጨቅላ ልጃቸውን በከተማዋ ማዕከል እየገፋች በነበረችበት ወቅት በባለቤቷ ሃቢቡር ማሱም መወጋቷ የተገለጸ ሲሆን ልጃቸው አልተጎዳም።

ግድያው ባለፈው ዓመት የተፈጸመ ሲሆን ግለሰቡ በብራድፎርድ ፍርድ ቤት በግድያ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት ባለፈው ወር ነበር።

ማክሰኞ ዕለት የብራድፎርድ ፍርድ ቤት ግለሰቡ ቢያንስ 28 ዓመት እንዲታሰር ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት ዳኛ ጀስቲስ ኮተር "በጭካኔ እና ያለ ርህራራሄ" ባለቤቱን ኩሉሱማን 26 ጊዜ በስለት ወግቶ እንደገደላት ተናግረዋል።

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሁፍ በርካቶችን ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝሮችን ይዟል

"ከኪስህ ስለት አውጥተህ አላፊ አግዳሚ እያየህ ጥቃት ፈጽመህባታል" ሲሉ ዳኛው በብያኔው ወቅት ተናግረዋል።

ዳኛው እንዳሉት ግለሰቡ ሆነ ብሎ አቅዶ አንገቷን በስለት በተደጋጋሚ ከወጋት በኋላ "ጉሮሮዋን ከመቁረጡ በፊት" "እንደተረገጣት" በዝርዝር ተናግረዋል።

"በተደጋጋሚ በስለት ያደረስክባት ጥቃት በህይወት እንዳትተርፍ ያደረጋት ሲሆን የአንተም አላማ ይኸው ነበር" ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት የሃገር ውስጥ ጽህፈር ቤት ከባንግላዴሽ የመጣው ጥቃት ፈጻሚ ቀኑ ከመድረሱ በፊት ከእንግሊዝ መባረር ይችል እንደሆነ እንደሚገመግም ሰምቷል።

ግለሰቡ በቤድፎርድሻየር ዩኒቨርስቲ የእንግሊዝኛ ስነ ጽሁፍ ያጠና ሲሆን የመጣውም በድህረ ምረቃ ቪዛ ነበር። ቪዛው ሰኔ 13/ 2017 ዓ.ም ቢጠናቀቅም፤ በዩኬ ቢያንስ 36 ወራት መቆየት እንደሚችል ተገልጿል።

ግለሰቡ ኦልድሃም በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ስለት በጉሮሮዋ ላይ በማድረግ ካስፈራራት በኋላ ከጥር ወር ጀምሮ ከቤታቸው ወጥታ ለሴቶች ጥበቃ በሚሰጥ መጠለያ ውስጥ እንደነበረች ፍርድ ቤቱ ሰምቷል።

ሃቢቡር በባለቤቱ ላይ ጥቃት ከማድረሱ በፊት ባሉ ቀናት እሷ በምትኖርበት መጠለያ አካባቢ ባሉ ጎዳናዎች "ሲያንዣብብ፣ ሲከታተል እና ሲጠብቅ" መቆየቱንም በችሎቱ ተነግሯል።

አክታር ወደ ቤት የማትመለስ ከሆነ የቤተሰብ አባላትን እንደሚገድል የሚያስፈራራ መልዕክቶችን መላኩም ተሰምቷል።

ግለሰቡ መልዕክቶቹን በሚልክበት ወቅት ሌላ አገር እንደሆነ ባስመሰለ መልኩ ሊያታልላት መሞከሩ ተገልጿል።

እሷም አገር ውስጥ የለም ስፔን ነው በማለት ጓደኛዋን ለማግኘት መጠለያውን ለቃ እንደወጣች ተነግሯል።

ባለቤቷ የት እንዳለች ለማወቅ የስልኳን መተግበሪያ ተጠቅሞ በከማዋ ማዕከል እንደሄደና ባገኛትም ጊዜ ቢያንስ 25 ጊዜ በስለት ወግቷታል።

የአካባቢው የደህንንት፣ ሲሲቲቪ ቪዲዮ እንዳሳየው ግለሰቡ በተደጋጋሚ በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደላት በኋላ ተረጋግቶ ሲራመድ ያሳያል።

ከፖሊስም ለማምለጥ ወደ በኪግንግሃምሻየር እያቀና እንደነበር ተገልጿል።

ግለሰቡ በአውቶብስ ሲሳፈርም ፈገግ ብሎ እንደነበር ፍርድ ቤቱ ሰምቷል።

ሃቢቡር ባለቤቱን ከገደለ ከቀናት በኋላ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን የተከሰሰበትን የግድያ ወንጀል አምኗል።