ካማላ ሃሪስ ለቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በይፋ የዴሞክራቶች ዕጩ ሆነው ቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ነቀታዩ ምርጫ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነው በይፋ ተሰየሙ።
ኅዳር 2017 ዓ.ም. በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ካማላ ሃሪስ ከቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር አሜሪካን ለቀጣይ አራት ዓመታት ለመምራት ይፎካከራሉ።
ካማላ ይህን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን አዲስ ታሪክ ይጽፋሉ።
በቺካጎ በተደረገው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የፓርቲውን ዕጩነት በተቀበሉበት ንግግራቸው “የሁሉም አሜሪካውያን ፕሬዝዳንት” ለመሆን እሠራለሁ ብለዋል።
ካማላ በንግግራቸው ለአሜሪካውያን ዕድል የሚፈጥር ምጣኔ ሃብት ለመገንባት እንዲሁም አከራካሪው የጽንስ ማቋረጥ መብት እንዲረጋገጥ እሠራለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
“አገሬን በሙሉ ልቤ ነው የምወደው። በየሄድኩበት የማገኛቸው ሰዎች ወደፊት መጓዝ እንደሚፈልጉ ነው የሚነግሩኝ። አስደናቂው ጉዟችን አሁን ይጀምራል” ያሉት ካማላ አሜሪካውያን ከሚለያይዋቸው ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው ብዙ መሆኑን በማስታወስ ለአንድነት ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የካማላ ሃሪስን ንግግር ሲከታተሉ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ትራምፕ ምክትል ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው እንደ “የድንበር ጉዳይ፣ የዋጋ ግሽበት እና የወንጀል መጨመር” የተመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ከማውራት ይልቅ ስለ “አስተዳደጓ ብዙ እያወራች ነው” ሲሉ ተችተዋል።
ካማላ በንግግራቸው በልጅነታቸው አንዲት ጓደኛቸው የተፈጸመባት ፆታዊ ጥቃት እንዴት የሕግ ትምህርት እንዲከታተሉ መነሳሳት እንደሆናቸው እንዲሁም ወላጅ እናታቸው ኢፍትሃዊነትን እንዲዋጉ እንዴት እንዳስተማሯቸው በማብራራት የሕይወት ተሞክሯቸውን አጋርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ካማላ “አስደሳች” ስለነበረው የልጅነት ጊዜያቸው ከተናገሩ በኋላ፤ እናታቸው እንዴት ያበረታቷቸው እንደነበረ፣ ታላቅ እህታቸው እንዴት ይንከባከቧቸው እንደነበረ እና ወላጅ አባታቸው ደግሞ ሕልም ለማሳካት “ሩጫ” እንዳያቆሙ ይነግራቸው እንደነበረ ተናግረዋል።
የቢቢሲው የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ አንተኒ ዘርከር አሜሪካውያን ካማላ ሃሪስን የሚያውቁ ቢሆንም ምክትል ፕሬዝዳንቷ ዋይት ሐውስ ቢገቡ ምን ለመሥራት እንዳቀዱ በርካቶች ላያውቁ ይችላሉ ይላል።
ሃሪስ የልጅነት ጊዜያቸውን እና የስደተኛ ልጅ መሆናቸውን የተናገሩት መራጮች ማንነታቸውን እንዲያውቁ ያደረጉት ጥረት ነው ይላል።
በተያያዘ ዜና የዴሞክራቶች ጉባኤ እየተካሄደ ከነበረበት አዳራሽ ፊት ለፊት ድጋፋቸውን ለፍልስጤማውያን ያደረጉ አሜሪካውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር።
“ድል ለፍልስጤማውያን” የሚል መፈክር ይዘው የወጡት ተቃዋሚዎች በከፍተኛ ቁጥር በተሰማሩ የፖሊስ አባላት ተበትነዋል።
ተቃዋሚዎቹ ተወካያቸው በዴሞክራቶች ጉባኤ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ያቀረቡት ጥያቄ በካማላ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ውድቅ ተደርጓል።












