የትራምፕ መኖርያ ቤት በፖሊስ መፈተሹን ተከትሎ የፀጥታ አካላት እንዳይገደሉ ተፈርቷል

ባለፈው ሳምንት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤት (ማር ኤ ላጎ) ላይ ድንገተኛ አሰሳና ፍተሻ ተደርጎበት ነበር።

ይህን ተከትሎ በአሜሪካ የፀጥታ አካላት ላይ ስጋት ነግሷል።

በድርጊቱ የተቆጡ የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ ኃይል አባላትን እያስፈራሩ ነው።

የአሜሪካ የፀጥታ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለባልደረቦቻቸው ባስተላለፉት የተጠንቀቁ መልዕክት ‘አደጋ እንደተደቀነባችሁ አውቃችሁ በጥንቃቄ ተንቀሳቀሱ’ ሲል ያሳስባል።

ከዚህ የትራምፕ መኖሪያ ቤት ፍተሻ በኋላ በተለይም በፖሊሶች፣ በዳኞች፣ በዐቃቤ ሕግ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው የግድያ ዛቻ በእጥፍ ጨምሯል።

ባለሥልጣናቱ በዚህ የተጠንቀቁ ማሳሰቢያቸው ሁሉም የፀጥታ አባላት ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል አካባቢያቸውን በንቃት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

ኤፍቢአይ የአንድን የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ቤት ዘልቆ ገብቶ ብርበራ ሲያደርግ ትራምፕ የመጀመሪያው ናቸው።

በፍሎሪዳ ፓልም ቢች የባሕር ዳርቻ የሚገኘው የዶናልድ ትራምፕ ማር ኤ ላጎ መኖርያ ቤት ድንገተኛ ብርበራ ከተደረገበት በኋላ በርካታ ሰነዶች ማግኘቱን የአሜሪካ ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ ተገኙ ከተባሉ ሰነዶች መካከል በዶናልድ ትራምፕ ቤት በፍጹም መገኘት ያልነበረባቸው ጥብቅ የአገር ምሥጢሮች ይገኙበታል ተብሏል።

የአገር ምሥጢሮች ‘ጥብቅ ምሥጢር’፣ ምሥጢር እና ለሕዝብ ያልተፈቀደ በሚል ይከፈላሉ።

ጥብቅ የአገር ምሥጢር ተደርገው ከተቀመጡ ሰነዶች መካከል ደግሞ እጅግ ጥብቅ የአገር ምሥጢር ተብለው የተሰነዱ ይገኙበታል።

እነዚህ ሰነዶች በአሜሪካ አስተዳደር ውስጥ ሦስት እና አራት የተመረጡ የደኅንነት ሰዎች ብቻ ሊያውቋቸው የሚገቡ ፍጹም ምሥጢር ሆነው መቆየት የነበረባቸው ናቸው ተብሏል።

እነዚህ ሰነዶች ለምን በዶናልድ ትራምፕ ቤት ተገኙ የሚለውን ፖሊስ እየመረመረ ነው።

ትራምፕ በበኩላቸው እነዚህ ዶሴዎች ቀድሞውንም ከምሥጢራዊ ሰነድነት ሰንዱቅ እንዲወጡ መደረጋቸውን ይናገራሉ።

ይህን ውዝግብ ተከትሎ የዶናልድ ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች ትራምፕ ራሳቸውን በሚያስተዳድሩት የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች ጭምር በመጠቀም ለፖሊሶችና የፀጥታ አካላት የግድያ ዛቻ እያደረሱ ነው።

እነዚህ ዛቻዎች ዛቻ ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ ባለፈው አርብ በኦሃዮ ግዛት የኤፍቢአይ ቢሮን ጥሶ ጥቃት ሊፈጽም የነበረ አንድ ወጣት በፖሊስ ተገድሏል።

ሟች ይህን የግድያ ሙከራ ከማድረጉ በፊት 'ትሩዝ ሶሻል' በሚባለው የትራምፕ ማኅበራዊ የትስስር መድረክ ላይ የፀጥታ አካላትን ለመግደል እንደተዘጋጀ ጽፎ ነበር።

አንዳንድ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ይህ በትራምፕ ላይ እየተደረገ ያለው ማሳደድ እሳቸውን በቀጣይነት ዳግም ወደ ሥልጣን እንዳይመጡ ለማሸማቀቅ በዲሞክራቶች የተጎነጎነ ሴራ ነው ብለው ሲተቹ ቆይተዋል።

ይህ ትችት እየሰፋ በመሄዱ ፖሊስ በፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ ያገኘበትን ማስረጃ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ተገዷል።

ከዚህ ቀደም ፖሊስ አንድ ምርመራ ሳይገባደድ ለፍርድ ቤት ብርበራ እንዲያካሄድ እንዲፈቀድለት ያቀረባቸውን መረጃዎች ለሕዝብ ይፋ አያደርግም ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ብርበራውን ተከትሎ ሦስት ፓስፖርቶቼ ተወስደውብኛል ብለዋል።

ብርበራውን ተከትሎ በተገኙ ሰነዶች ትራምፕ አዲስ ክስ ይከፈትባቸው እንደሆነ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።

ትናንት ሰኞ ምሽት ዐቃቤ ሕግ የዶናልድ ትራምፕ ወዳጅና ጠበቃ ሩዲ ጁሊያኒን ለመክሰስ ሰነዶች እየሟሉ እንደሆነ ተዘግቧል።