በአርጀንቲና አንድ ደጋፊ ከስታድየም ወድቆ መሞቱን ተከትሎ ጨዋታ እንዲቋረጥ ተደረገ

ጨዋታው እንዲቋረጥ ተደረገ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጨዋታው እንዲቋረጥ ተደረገ በኋላ

በአርጀንቲና ከፍተኛው የእግር ኳስ ሊግ ግጥሚያ በአንድ ደጋፊ ሞት ምክንያት እንዲቋረጥ ተደረገ።

ፕሪሚዬራ ዲቪዥን በተሰኘው የአርንጀቲና ሊግ መሪ የሆነው ሪቨር ፕሌት ከዲፌንሳ ዋይ ጀስቲሲያ ግጥሚያውን እያደረገው ነበር።

ዋና ከተማዋ ቦዌኖስ አየርስ በሚገኘው ግዙፉ ሞኑመንታል ስታድየም ነበር ጨዋታው የተካሄደው።

ነገር ግን የጨዋታው ዳኛ ፈንናንዶ ራፓሊኒ በተፈጠረው አደጋ ምክንያት ግጥሚያው እንዲቋረጥ ሲያዙ ፖሊስ እና የእሣት አደጋ ሠራተኞች ወደ ሜዳው ብተዋል።

የሪቨር ፕሌት ባለሥልጣናት ደጋፊው “እዚያው ሜዳ ውስጥ ነው የሞተው” ብለዋል።

አክለውም ደጋፊው የሞተበት ምክንያት በተጨማሪ ምርመራ እንደሚጣራ ጠቁመዋል።

ስታደየሙ ለ24 ሰዓታት ያክል ዝግ ሆኖ ማስረጃ እንደሚሰበሰብ የክለቡ አመራሮች ገልጸዋል።

“የጤና ሙያተኞች ወደ አደጋው ሥፍራ በፍጥነት ነው የደረሱት። ፖሊስ እና ሌሎች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቶሎ ወደ ሥፍራው መምጣታቸውን ተመልክተናል” ይላል የክለቡ መግለጫ።

“ሲቮሪ አልታ የተባለው የስታድየሙ ክፍል 90 በመቶ ሞልቶ ነበር። ደጋፊው ወድቆ ሲሞት ሦስተኛ አካል አልተሳተፈም። አደጋው በተፈጠረበት ሥፍራም ግርግርም ሆነ ግጭት እንዳልነበር ተጣርቷል” ሲል መግለጫው አክሏል።

ክለቡ ቆየት ብሎ እንደገለጠው የደጋፊው ስም ፓብሎ ማርሴሎ ሴራኖ ነው።

“ዛሬ ከባድ ሐዘን ላይ ነን” ያለው ሪቨር ፕሌት በአደጋው የተሰማውን ሐዘን ገልጾ “ለቤተሰቦቹ እና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናት እንመኛለን” ብሏል።