በአማራ ክልል በፀጥታ ኃይሎች እና በነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ

ካርታ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም፣ ጂጋ እና ደምበጫ ከተሞች በፀጥታ ኃይሎች እና በወጣቶች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጹ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፍኖተ ሰላም ሰላም ነዋሪ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ሌላ ግጭትን ተከትሎ መሆኑን አስረድተዋል።

ነዋሪው በፍኖተ ሰላም የፀጥታ ችግሩ የተቀሰቀሰው ከትናንት በስተያ ሰኞ ሰኔ 05/2015 ዓ.ም. ቀትር ላይ እንደሆነ ጠቅሰው የክስተቱ መነሻ በደምበጫ ከተማ ያጋጠመው “የሰዎች ሕይወት ያለፈበት” ግጭት መሆኑን ነዋሪ ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ በከተማዋ እሳቸው “ሕዝባዊ ተቃውሞ” ሲሉ የገለጹት ክስተት መፈጠሩን እና በሰዎች ላይ በጥይት ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

“መከላከያ ወደ ፍኖተ ሰላም እየመጣ ነው የሚል ወሬ ተናፍሶ ነበር። ስለዚህ መከላከያ ወደ ፍኖተ ሰላም ከመጣ ልክ የደንበጫ ዕጣ ፈንታ ይደርሳል በሚል ምሳ ሰዓት ላይ ወጣቶች ተሰባስበው ወደ ከተማዋ የሚያስገባውን መስመር ዘጉት። ከዚያ በኋላም አልፈው የባሕር ዳር መውጫ እና መግቢያውን ዘጉት” ብለዋል።

ነዋሪዎች ‘መከላከያ ወደ ከተማው መግባት የለበትም’ እንዲሁም ‘ፋኖ ትጥቅ መፍታት የለበትም’ የሚል ድምጽ ማሳማቱንም አመልክተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እኚሁ ነዋሪ “በሰላማዊ መንገድ ነዋሪዎች ሀሳባቸውን እየገለጹ” ባለበት ወቅት አንድ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል “ሕዝቡ ላይ ተኩሶ ጉዳት አደረሰ” ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የከተማው ፖሊስ በከፈተው ተኩስ ስምንት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ገልጸዋል።

የፍኖተ ሰላም ነዋሪው መከላከያ ወደ ከተማው አለመግባቱን ጠቅሰው፣ ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 06/2015 ዓ.ም. ወደ ባሕር ዳር እና ኮሶ በር የሚወስዱ መንገዶች ተከፍተው የሰዎች እና የመኪና እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ተናግረዋል።

በጂጋ ከተማ የሚገኙ ነዋሪ ደግሞ በከተማቸው ወጣቶች በመታሰራቸው ምክንያት ከትናንት በስትያ ሰኞ ሰኔ 05/2015 ዓ.ም. ተቃውሞ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሆኖም በሃይማኖት አባቶች እና በሽማግሌዎች በተደረገ ጥረት ወጣቶቹ በመፈታታቸው ከተማዋ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሷን ተናግረዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዘመኑ ታደለ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ቢቆጠቡም ችግሩ እንደተፈጠረ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ኃላፊው በፍኖተ ሰላም፣ በጂጋ እና በደምበጫ ከተሞች “መንግድ የመዝጋት እና እንቅስቃሴ የማቆም ሁኔታ” ነበር ብለዋል።

አቶ ዘመኑ የዚህ መነሻ ከፀጥታ አካላት ጋር የነበረ አለመግባባት ነው ካሉ በኋላ፣ ዝርዝር መረጃ አሁን መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ደንበጫ ላይ ዕሁድ ሰኔ 04/2015 ዓ.ም. ማምሻውን ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር የተፈጠረ አለመግባባት “የእንቅስቃሴዎቹ” መነሻ እንደሆነ አስረድተዋል።

በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር አቅራቢያ በሚገኙት በእነዚህ ከተሞች የተፈጠረው ችግር ተረጋግቶ ከማክሰኞ ጀምሮ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደተመለሱ ኃላፊው ተናግረዋል።

ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ደግሞ በተለይ በደንበጫና ፍኖተ ሰላም ሦስት ሰዎች መገደላቸውን በከተሞቹ የሚገኙ ሆስፒታሎች እና ነዋሪዎችን ጠቅሰው ዘግበዋል።