ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጦር ወንጀል የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት የነበረው ኢራናዊ በእስረኛ ልውውጥ ነጻ ወጣ
በስዊድን በጦር ወንጀል የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት የነበረው ኢራናዊ በሁለቱ አገራት መካከል በተገደረገ የእስረኛ ለውውጥ ነጻ ወጣ።
የዕድሜ ልክ የእስር ቅጣቱን በስዊድን እስር ቤት እያሳለፈ የነበረው ሃሚድ ኑሪ በሁለት እስረኞች ተለውጦ ወደ ኢራን ተልኳል።
በምላሹ በኢራን እስር ቤቶች ውስጥ የነበሩት ዲፕሎማቱ ጆሃን ፍሎደርስ እንዲሁም የኢራን እና የስዊድን ጥምር ዜግነተ ያለው ሳኢድ አዚዚ ትናንት ቅዳሜ አመሻሽ ስቶኮልም ደርሰዋል።
ኢራናዊው ኑሪ እአአ 2019 ላይ በስዊድን በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በኢራናዊያን የፖለቲካ እስረኞች ላይ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ ተሳታፊ በመሆኑ ጥፋተኛ ተብሎ ነበር።
ዲፕሎማቱ ፍሎደርስ ደግሞ ከሁለት ዓመታት በፊት በስለላ ወንጀል ክስ ተመስርቶበት በኢራን በእስር ላይ ቆይቷል።
ጥምር ዜግነት ያለው አዚዚ ደግሞ ባለፈው ሕዳር ፍርድ ቤት ቀርቦ አምስት ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ ተፈርዶበት ነበር።
ስዊድን በኢራናዊው ግለሰብ ላይ የዕድሜ ልክ እስራት ከፈረደች በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል።
የእስረኛ ልውውጡን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡለፍ ከሪስቴርሰን ኢራን ሃሚድ ኑሪን ነጻ ለማውጣት ሁለቱን ስዊድናውያንን ማሰሯን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሚድ ኑሪ “በ1980ዎቹ በኢራን በተፈጸመ ከባድ ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ” ነው በማለት “ወንጀለኛውን” ነጻ ለማውጣት በሁለቱ ስዊድናውያን ላይ የሐሰት ክስ ተመሰርቷል ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢራን የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ካውንስል ጸሐፊ ካዚም ጋሃሪባባዲ በኤክስ ገጻቸው ላይ በስዊድን “በሕገ-ወጥ” መንገድ ታስሮ የነበረው ኑሪ አሁን ነጻ ወጥቷል ብለዋል።
እንደ የስዊድን ዐቃቤ ሕግ ከሆነ ኑሪ እአአ 1988 ላይ በኢራኑ ጎሃርዳሸት እስር ቤት ሠራተኛ ሳለ የጦር ወንጀሎችን ፈጽሟል።
በወቅቱ ለኢራን አስተዳደር ጠላት ናቸው የተባሉ በእስር ቤቱ የነበሩ ከ2 ሺህ 800 እስከ 5 ሺህ ሰዎች በሃይማኖታዊ መሪው አያቶላህ ኬይሚኒ ትዕዛዝ መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይገምታሉ።
ኑሪ ከጥቂት ዓመታት በፊት በስዊድን በቁጥጥር ስር የዋለው ከኢራን በተነሳ አውሮፕላን ተሳፍሮ ስቶኮልም ከደረሰ በኋላ ነው። የ63 ዓመቱ ግለሰብ የሚቀርቡበትን ክሶች ያጣጥላል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ በቀረቡበት ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ ያለፉትን ጥቂት ዓመታት በስዊድን እስር ቤት ቆይቷል።
የ33 ዓመቱ ዲፕሎማት ፍሎደርስ ደግሞ ለሽርሽር ባቀናበት ወቅት በስለላ ወንጀል እአአ 2022 ላይ ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ የሞት ቅጣት ሊተላለፍበት ይችላል ተብሎ ተስግቶ ነበር።
በ60ዎቹ የዕድሜ መጀመሪያዎቹ ላይ የሚገኙት የኢራን እና ስዊድን ጥምር ዜግነት ያላቸው አዚዚ ደግሞ በብሔራዊ ደኅንነት ሰዎችን በማደራጀት ተከሰው ነበር።
ይህ የእስረኛ ለውጥ እንዲደረግ ኦማን ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቷ ተነግሯል።