መካከለኛ አፍሪካ ሪፓብሊክ ቢትኮይንን ይፋዊ መገበያያ አደረገች

ቢትኮይን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

መካከለኛ አፍሪካ ሪፓብሊክ ቢትኮይንን ይፋዊ መገበያያ በማድረግ ሁለተኛዋ አገር ሆነች።

ቢትኮይንን አገር አቀፍ መገበያያ በማድረግ ኤል ሳልቫዶር የመጀመሪያዋ ናት።

የሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ ሕግ አውጭዎች በሙሉ ድምጽ ቢትኮይን መገበያያ እንዲሆን ውሳኔ አሳልፈዋል።

"ውሳኔው አገሪቷን ከዓለም ባለ ራዕይ አገሮች አንዷ ያደርጋታል" ብለዋል።

ከአለማችን ድሃ አገራት አንዷ ብትሆንም በአልማዝ፣ ወርቅና ዩራንየም የበለጸገች ናት።

የሩሲያ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ (ካር) ለዓመታት በግጭት ስትናጥ ቆይታለች።

የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በአገሪቱ አማጽያንን እየተዋጉ ነው የሚለው ዜና ከወራት በፊት መውጣቱ አይዘነጋም።

ኤል ሳልቫዶር እአአ መስከረም 2021 ላይ ቢትኮይንን መገበያያ ስታደርግ አይኤምኤፍን ጨምሮ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ውሳኔውን ተችተዋል።

ቢትኮይንን ይፋዊ መገበያያ ማድረግ የፋይናንስ ሥርዓት አለመረጋጋት ይፈጥራል፣ ወንጀለኞች ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲያስገቡ መንገድ ይከፍታል፣ ሂደቱ በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለሚወስድም አካባቢ ይበክላል ብለው ነበር የነቀፉት።

የ2019 መረጃ እንደሚያሳየው፣ ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ከአጠቃላይ ሕዝቡ 4 በመቶ ናቸው።

ይህም ቢትኮይንን ለመጠቀም ፈታኝ ያደርገዋል።

በአገሪቱ ጥቅም ላይ የሚውለው በፈረንሳዩ ሲኤፍኤ ባንክ የሚደገፈው ፍራንክ ነው።

ባንኩ በማዕድን የበለጸገችው አገር ላይ የበለጠ ጫና እንዳያሳድር በሚል አገሪቱ ወደ ቢትኮይን ፊቷን አዙራለች የሚሉ አሉ።

ቴሪ ቪርኮሉን የተባሉ ተንታኝ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ ያለው መዋቅራዊ ሙስና እንዲሁም የአገሪቱ ወዳጅ አገር ሩሲያ ከሰሞኑ በምዕራባውን ማዕቀብ ሥር መውደቋ፣ ቢትኮይንን መገበያያ ለማድረግ እንዲወሰን ሳይገፋፉ አልቀሩም።

በመዲናዋ ባኑጊ የሰዎች ስሜት የተደበላለቀ ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ያን ዳውሮ፣ በቢትኮይን መገበያየት ሕይወትን ቀላል ያደርጋል ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየት ሰጥተዋል።

"ነጋዴዎች ከዚህ በኋላ የሲኤፍኤ ፍራንክ ይዘው መጓጓዝ የለባቸውም። በቢትኮይን በስልክ መገበያየት ይቻላል። ቢትኮይንን ወደ ሌላ መገበያያ ገንዘብ በቀላሉ መቀየርም ይቻላል" ብለዋል።

ሲኤፍኤ አፍሪካን የሚጠቅም አሠራር እንዳልዘረጋ ባለሙያው ይናገራሉ።

ሌሎች የፈረንሳዩ ባንክ ጥገኛ የሆኑ የአፍሪካ አገራት መገበያያውን እንዲተውት የሚጠይቁም አሉ።

መገበያያው ከቅኝ ግዛት የተወረሰና ፈረንሳይ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና እንድታደርግ የሚረዳት ነው በሚል ይተቻል።

ኮምፒውተር ሳይንቲስቷ ሲድኒ ቲካያ በበኩሉ፣ ቢትኮይንን መገበያያ ማድረግ ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው ሲል ይከራከራል።

"የኢንተርኔት ዝርጋታ ውስን ነው። ቢትኮይን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ኢንተርኔት ላይ የተመሠረተ ነው። ወደ ቢትኮይን የመሸጋገሪያው ጊዜ አሁን አይደለም" ብሏል።

አገሪቱ እንደ ትምህርት እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያሉ መሠረታዊ አቅርቦቶችን ማሟላት ላይ ብታተኩር እንደሚሻልም ይመክራል።

ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣት በኋላ ከ1960ዎቹ ወዲህ በግጭት ስትናጥ ቆይታለች።

በ2013 ሙስሊም አማጽያን በብዛት የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የሚገኙባትን አገር ተቆጣጠሩ።

ይህንን በመቃወም ሚሊሻዎች መደራጀት ጀመሩ። ይህም በሃይማኖት የተከፋፋለ ግጭትን አስከተለ።

2016 ላይ ፕሬዝዳንት ፋውስቲን አርቻንጌ ቶዋድራ ሥልጣን ከያዙ በኋላ አገሪቱ ከፈረንሳይ ወደ ሩሲያ ወዳጅነት ተሻግራለች።