ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"እንደ ፋኖ ያሉ አደረጃጀቶች ከምዕራብ ትግራይ መውጣት አለባቸው" አምነስቲ
ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ፣ የትግራይ ተወላጆች ላይ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል የሚል ሪፖርት አውጥተዋል።
የዚህን ሪፖርት መውጣት ተከትሎ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ አጥኚ ለሆኑ አቶ ፍስሃ ተክሌ ቢቢሲ ጥያቄዎችን ሰንዝሯል።
ቢቢሲ፡ የትግራይ ሃይሎች ብሎም የተለያዩ ትግራይ ክልል ላይ ያተኮሩ የአክቲቪዝም ስራ የሚሰሩ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች በምዕራብ ትግራይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) እንጂ የዘር ማጽዳት አይደለም ሲሉ ይደመጣል። የእናንተ ሪፖርት የዘር ማጽዳት ተፈጽሟል የሚለውን ድምዳሜ ወስዷል። ይህ ድምዳሜ ላይ እንዴት ደረሳችሁ?
አቶ ፍስሃ፡ እንግዲህ ይህ የዘር ማጥፋት ክስ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ጦርነት ውስጥ በሰፊው ይነሳል። ነገር ግን እኛ ሪፖርታችንን የምናዘጋጀው በሰበሰብነው ማስረጃ ላይ ተመስርተን ነው። ለዚህ ሪፖርት የሰበሰብነው ማስረጃ የሚያሳየው አካባቢውን ከአንድ ብሔር የማጽዳት ተግባር እንጂ ዘር ማጥፋት እንዳለ የሚያሳይ መረጃ የለንም።
ያ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ ይሄ ነገር የለም ማለት ሳይሆን ቦታው ላይ ተገኝቶ ምርመራ ማድረግ ቢቻል እዛም ደረጃ ጋር የሚደርስ ነገር ሊገኝ ይችላል። ነገር ግን እኛ መናገር የምንችለው ባለን መረጃ መጠን ነው። ይህ ነገር አልተፈጠረም ብለን እያረጋገጥን ሳይሆን ባለን መረጃ ላይ ተመስርተን የተፈጸሙ ወንጀሎች አካባቢውን ከአንድ ዘር የማጽዳት ነው ያልነው። ይሄ ማለት ግን የተፈጸሙት ወንጀሎች ቀላል ናቸው እያልን አይደለም።
ወደ ጄኖሳይድ ስንመጣ በአለም ላይ ትልቁ ወንጀል ይመስላል። ነገር ግን በአለማቀፍ ወንጀል ላይ የወንጀል ተዋረድ ወይም መሰላል የሚባል ነገር የለም። በአለማቀፍ ወንጀል ላይ የተቀመጡት አራት ወንጀሎች ናቸው። በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የጦር ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት እና ወረራ ናቸው። እነዚህ በሙሉ ከባድ ሰለሆኑ ነው እዚህ ውስጥ የተቀመጡት ብሎም አንዱ አንዱ ከአንዱ አይበልጥም።
የዘር ማጽዳት በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ውስጥ የሚካተት ሲሆን እነዚህ ወንጀሎች በሙሉ ከዘር ማጥፋት እኩል ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው።
ቢቢሲ፡በሪፖርታችሁ ውስጥ አለማቀፍ አጋሮች ያላችሁት ኤርትራን ብቻ ነው ወይስ የሌሎች አገሮችን ተሳትፎ ተመልክታችኋል? ምዕራብ ትግራይን በሚመለከት?
አቶ ፍስሃ፡ በአካል በቦታው ተገኝቶ ተሳትፎ አላቸው የምንላቸው አገራት የሉም፤ ከኤርትራ ወታደሮች ውጪ። የኤርትራ ሰራዊት አካላት ከጦርነቱ ጅማሮ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር ሆነው ሲዋጉ ነበር። በተለይም ከከባድ መሳሪያ ድብደባ ጋር ተያይዞ ኦምሃጂር ተብሎ ከሚታወቀው የኤርትራ ግዛት አካባቢ ድብደባ ሲያካሂዱ እንደነበር ይታወሳል። በሌሎች አካባቢ ገብተው የተለያዩ የመብት ጥሰት መሳተፋቸው ይታወሳል። ስለዚህም በዚህ ሪፖርት ማለት የፈለግነው የኤርትራ ሰራዊትን ነው።
ቢቢሲ፡ በሪፖርታችሁ መንግስት ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ያፍርስ ብላችሁ ጠይቃችኋል። ጦርነቱ በሁለቱም ወገን በኩል አሁን ያለበት ሁኔታ ይታወቃል። ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ መጠየቃችሁ እንዳለ ሆኖ እንደ ፋኖ ያሉ አደረጃጀቶች ይፍረሱ የሚለው ምክረ ሃሳብ ምን ያህል ሊፈጸም የሚችል ነው?
አቶ ፍስሃ፡ እንዲህ አይነት ምክረ ሃሳቦች ሁል ግዜ የሚሰጡ ወይም አቋም የምንወስድባቸው አይደሉም። በቀላሉም የሚደረስባቸው አይደሉም። ነገር ግን ካለው ሁኔታ አንጻር እና እንደ ፋኖ ያሉ የሚሊሻ አደረጃጀቶች ከፈጸሙት የመብት ጥሰቶች አንጻር በምዕራብ ትግራይ አካባቢ ላሉ በተለይም እስር ላይ ላሉት የትግራይ ተወላጆች የእነዚህ ሃይሎች እዛ መቆየት ከፍተኛ አደጋ ነው። እነዚህ ሃይሎች ከአካባቢው መውጣት አለባቸው። በሌሎች አካባቢዎች የፈጸሟቸውን የመብት ጥሰቶችን ስለምናውቅ እነሱ እስካሉ ድረስ ከባድ የሆነ አደጋ ስላለው ነው ትጥቃቸውን ፈትተው ይበተኑ ያልነው።
ቢቢሲ፡ ሌላኛው ምክረ-ሃሳብም እንዲሁ ያልተለመደ እና ትልቅ ነው። የሰላም አስከባሪ ሀይል ይግባ የሚል። ይህንን ሃሳብ እንዲገቡ ምክረ ሃሳብ ላይ ለተጠቀሱት ተቋማት አቅርባችኋል?
አቶ ፍስሃ፡ ሌላው ትልቁ እንዲሁም ያልተለመደው ምክረ ሃሳባችን ይህ የሰላም አስጠባቂ ሃይል ይስፈር የሚለው ነው። ይህ ግን በሁለቱ አካላት ስምምነት ብሎም በአፍሪካ ሕብረት ተመርቶ ይግባ የሚል ነው። ይህንን ያልነው በምዕራብ ትግራይ ያለውን እሰጥ አገባ ስለምንረዳ ነው። በብዙ መልኩ ሁለቱም ወገኖች የሚከራከሩበት አካባቢ ሲሆን ለረጅም ግዜ ችግሩ ሳይፈታ ቆይቶ ነው አሁን ጦርነቱን ተክተሎ ችግሮቹ የተበራከቱት።
ስለዚህ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ በቀላሉ የሚፈታ ነው ብለን አንገምትም። ከፍተኛ የሆኑ የጥቅም ግጭቶች ያሉበት ነው። ስለዚህ ይህ እስከሚፈታ ድረስ በአካባቢው ያለው የሲቪል ሕብረተሰብ በሁለቱም ወገን አደጋ ላይ አደጋ ላይ ወድቋል። ጦርነቱ በአካባቢው የሚከፈት ከሆነ በእስር ላይ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ለበቀል እርምጃ ሊዳረጉ ይችላሉ።
ጉዳዩ እልባት እስከሚሰጠው መጠበቅ ስለማይቻል እና ግዜም የሚፈልግ ነገር ስለሆነ ሲቪሎችን ለመከላከል ሊሆን የሚችለው አካል ይህ አለማቀፍ ወይም ቀጠናዊ የጸጥታ ማስጠበቅ ሃይል ነው። ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሰጠነው ምክረ ሃሳብ ነው።
በዚህ ጉዳይ የአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ያደረጉት ምንም አይነት እርምጃ የለም። የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የጸጥታ ኮሚሸን በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አጀንዳ አድርጎ ተወያየቶበት አያውቅም። የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም እንዲሁ ምንም ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ የለም።
ምክረ ሃሳቡን ያስቀመጥነው ሪፖርቱ ላይ ካለው ግኝት እና አሳሳቢ ሁኔታ በመነሳት ይህንን እንዲያስቡበት መነሻ ሃሳብ ለመስጠት ነው። ሪፖርታችንን ለተቋማቱ ከማስገባት በተጨማሪ የፊት ለፊት ውይይቶች ይኖሩናል ብለን አቅደናል።
ቢቢሲ፡ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ያለው የመሬት ጥያቄ ጦርነት በሌለባቸው በመላው ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎችም ሲነሳ የምንሰማው ነው። አካባቢው ላለፉት 3 አስርት አመታት የማንነት ጥያቄ ሲነሱበት የቆየ እና አሁን አካባቢውን በሚያስተዳድሩት ግለሰብ የሚመሩት እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የደረሰ ጥያቅም ነበረበት። ለሌሎች አካባቢዎች ላሉ ውጥረቶች በምዕራብ ትግራይ የደረሰው ቀውስ እና የመበት ጥሰት ምን ትምህርት ይሰጣል?
አቶ ፍስሃ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገ-መንግስት ከጸደቀ ጀምሮ እና አዲስ የአስተዳደር ወሰን ከተካለለ ጀምሮ በርካታ የማንነት እንዲሁም የመሬት ጥያቄዎች ይነሳሉ። ከሽግግር መንግስቱ የጀመሩት የራስን እድል በራስ መወሰን ጥያቄዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ጥያቄዎች አሉ።
ምዕራብ ትግራይ የአሁኑ ጉዳይ ቢሆንም በርካታ የቅርብ ግዜ ትዝታዎች አሉ። በአፋር እና በሶማሌ ማሃል ያለው ግጭት፣ በሲዳማ ክልል ለመመስረት የነበረው ብዙ ሰው የሞተበት ክስተት፣ ወላይታ እንዲሁም በጉጂ የሚነሱ መሰል ክስተቶችን ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ግጭቶች የችግሩ መገለጫ ናቸው።
ጥያቄዎቹ በሚነሱ ግዜ መልስ አልተሰጣቸውም። በሕገ-መንግስቱም ሆነ በሌላ መልኩ ዘላቂ መፍትሄ አላገኙም። ይልቁንም ጥያቄዎቹን በፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ በተለያየ መልኩ የሚያነሱ ወገኖችን በተለያየ ምልኩ በማሰር እና በመግደል ጥያቄዎቹን ለማፈን ይሞከር ነበር።
ምዕራብ ትግራይም ላይ እንደዚሁ ነው የቆየው። ከ 30 ዓመት በላይ የቆየ ጥያቄ አለ። ያ ጥያቄ ግን በፌዴሬሽን ምክር ቤትም የጠየቁ እንዲሁም በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ የተሰለፉ ሰዎች ሲገደሉ ነው የምናስታውሰው። እኤአ በ 2016 ጎንደር ላይ ብዙ ሰዎች መገደላቸውን እናስታውሳለን። እኤአ በ 2019 አምነስቲ ጎንደር ላይ ቃለ መጠይቆችን አድርጎ ነበር።
ከተለያዩ የወልቃይት አካባቢዎች ማለትም ከዳንሻ፣ ከማይካድራ፣ ከዲቪዥን፣ ከሁመራ፣ ከአዲጎሹ የመጡ ሰዎችን አናግረናል፤ በዚህ ሪፖርት ውስጥም አካተነዋል። አነዚህ ሰዎች ይህንን ጥያቄ በመጠየቃቸው ብቻ ነው ሲታሰሩ፣ ሲንገላቱ እና ከቤታቸው ሲፈናቀሉ ነው የኖሩት። አማርኛ ሙዚቃ እንኳን መስማት የማይችሉበት ሁኔታ እንደነበረ ነው የምናውቀው።
ምዕራብ ትግራይ ላይ የሰራነው ጥናት በትክክልም የሚያሳየው እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ እንዳለባቸው፤ ካልሆነ ግን የተጠመደ ቦምብ እንደሆነ እና መፈንዳታቸው እንደማይቀር ማሳያ ነው። መንግስት እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ አለበት። በመንግሰት በኩል የተደረጉ ጥረቶችን በሪፖርታችን አንስተናል። ለምሳሌ የአስተዳደር ወሰን ችግሮችን እንዲፈታ የተዋቀረው ኮሚሽንን የትግራይ ክልል አልተቀበለውም ነበር።