ጆ ባይደን የአፍጋኒስታን ወታደራዊ ተልዕኮ መቋረጡ ትክክል ነው አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአፍጋኒስታን የነበራቸውን ወታደራዊ ተልዕኮ ለማቋረጥ የተረገውን ውሳኔ እንደሚያምኑበትና በአውሮፓውያኑ ነሀሴ ወር መጨረሻ ላይ ወታደሮቹ ጠቅልለው ከአፍጋኒስታን እንደሚወጡ ገለጹ።

ይህንን ጦርነት ካስተናገዱ አራት የአሜሪካ መሪዎች መካከል አንደኛው የሆኑት ጆ ባይደን የወታደራዊ ተልዕኮው በፍጥነት እንዲቆም መደረጉን አስታውሰው በዚህ ምክንያት የበርካቶች ህይወት መትረፍ እንደቻለ ተናግረዋል።

ጆ ባይደን ይህንን ይበሉ እንጂ የአሜሪካና የኔቶ ወታደሮች ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ታሊባን በርካታ የአፍጋኒስታን አካባቢዎች በቁጥጥሩ ስር እያደረገ ነው።

የአሜሪካ ወታደሮች በአፍጋኒስታን 20 ዓመታት ለሚሆን ጊዜ የቆዩ ሲሆን የዚህ ወታደራዊ ተልዕኮ ዋነኛው ምክንያት በአውሮፓውያኑ 2001 መስከረም 11 በአሜሪካ መንታ ህንጻዎች ላይ የደረሰው የሽብር ጥቃት ነው።

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መስከረም 11፥ 2021 ላይ ወታደሮቹ ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው እንደሚወጡ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግንቦት 2021 ላይ ወታደሮቹን ለማስወጣት ከታሊባን ጋር ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም የአሁኑ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደደን ግን ቀነ ገደቡን ወደ ነሀሴ ወር ገፍተውታል።

''ተጨማሪ አንድ ዓመት በአፍጋኒስታን ጦርነት ላይ ማሳለፍ ተገቢ አይደለም'' ብለዋል ፕሬዝዳንት ባይደን ከዋይት ሃውስ ባስተላለፉት መልእክት።

ምንም እንኳን አሜሪካ ወታደሮቿን ሙሉ በሙሉ ጠቅልላ ለማስወጣት እየሰራች ቢሆንም ከ650 እስከ 1000 የሚደርሱ ወታደሮች ግን አፍጋኒስታን ውስጥ ይቀራሉ። ዋነኛ ስራቸውም የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ካቡሉ አየር ማረፊያን እና ወሳኝ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን መጠበቅ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም አስተርጓሚዎች፣ ረዳቶችና ሌሎች አሜሪካን ሲረዱ የነበሩ አፍጋኒስታናውያንን ለማስወጣት እየተሰራ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት እነዚህን ሰዎች ለማስተናገድ 2500 ልዩ የስደተኛ ቪዛ ተዘጋጅቷል።

በአፍጋኒስታን መንግስትና በታሊባን መካከል የመንግሥት ስልጣንን እንዴት መከፋፈል ይቻላል በሚለው ላይ ሲደረግ የነበረው ድርድር በጣም አዝጋሚ መሆኑን ተከትሎ የአሜሪካ ወታደሮች ከመውጣታቸው በፊት ስምምነት ላይ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

በርካቶች የአሜሪካ ወታደሮች መውጣታቸውን ተከትሎ ታሊባን በኃይል ነገሮችን ለመቆጣጠር ሊሞክር እንደሚችል እየተናገሩ ነው። ምክንያቱም የአፍጋኒስታን መንግሥት አሁንም ቢሆነ የአሜሪካ ወታደሮች የሚያደርጉለት ድጋፍ ከፍተኛ ነው።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአፍጋኒስታን ወታደሮች ከታሊባን ታጣቂዎች ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ ወደ ጎረቤት አገር ታጂኪስታን መሸሻቸውን ባለስልጣናት ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

ወታደሮቹ ድንበር ተሻግረው ያፈገፈጉት ሕይወታቸውን ለማዳን እንደሆነ የታጂኪስታን ድንበር ጥበቃ መስሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ ያትታል።

በአፍጋኒስታን ግጭትና ሞት እየተበራከተ የመጣ ሲሆን ታሊባን ደግሞ በርካታ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል። በተለይ ደግሞ በቅርብ ሳምንታት ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍሎችን ታሊባን በፍጥነት እየተቆጣጠረ ነው።

አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና የኔቶ አባል አገራት ከታሊባን ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት ሙሉ ወታደሮቻቸውን ለማስወጣት የተስማሙ ሲሆን በምላሹ ደግሞ ታሊባን ማንኛውም አይነት አክራሪ ቡድን አገራቱ በሚቆጣጠሩት አካባቢ እንዳይኖር ለመከላከል ቃል ገብቷል።

ነገር ግን ታሊባን በዚህ ስምምነት ላይ ከአፍጋኒስታን ወታደሮች ጋር አልዋጋም አላለም ነበር። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰአት አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል በታሊባን ቁጥጥር ስር ይገኛል።