ፕሬዝደንት ባይደን ማስካቸውን አውልቀው ይህ "ለአሜሪካ ታላቅ ቀን ነው" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Pool
በአሜሪካ የኮቪድ-19 ክትባት የወሰዱ ሰዎች የአፍ እና አፍንጫ ጭምብል የማድረግ ግዴታ የለባቸውም መባሉን ተከትሎ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ማስካቸውን አውልቀው ይህ ለአሜሪካ ታላቅ ቀን ነው ብለዋል።
ባለስልጣናት በአሜሪካ የኮሮናቫይረስ ክትባትን የወሰዱ ሰዎች ከውስን ቦታዎች በስተቀር ያለጭምብል መንቀሳቀስ ይችላሉ ብለዋል።
አካላዊ ርቀትን መጠበቅም አይጠበቅባቸውም ተብሏል።
ከዚህ ውሳኔ በኋላ "ኦቫል" ቢሮ ከሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች ጋር ፕሬዝዳንቱ ራሳቸው ያለጭምብል ታየተዋል።
ይሁን እንጂ እንደ አወቶብስ፣ አውሮፕላንና ሆስፒታል ባሉ መሰባሰብን በሚጠይቁ ከበር መለስ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው ቦታዎች ላይ ግን ክትባት የተከተቡትም ቢሆኑ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታቸው ነው።
ሙሉ በሙሉ ክትባቱን ላገኙ ሰዎች የኮቪድ ክልከላዎች እንዲነሱላቸው በባይደን አስተዳደር ላይ ጫና ሲደረግበት ቆይቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ የመምህራን ፌዴሬሽን ለፕሬዝዳንት ባይደን ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከፈቱ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ ጥሪ የተላለፈው ፋይዘር ያመረተውን ከትባት ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 15 ያሉ ህጻናት መከተብ እንዲችሉ ፍቃድ ከተሰጠ በኃላ ነው።
አሁን ላይ በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ተሰምቷል።
የአሜሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅም ግዴታቸ እንዳልሆነ አስታውቋል።
በቲውተር ገጻቸው ያልተከተቡ ሰዎች 'ማስክ' ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ያሳሰቡት ባይደን "ህጉ ቀላል ነው መከተብ ወይም እስከትከተቡ ጭምብል ማደረግ። ምርጫው የእናንተ ነው" ብለዋል።
በአሜሪካ 35 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ክትባት ያገኘ ሲሆን የ ጆ ባይደን አስተዳደር ይሄ ቁጥር እስከ ሀምሌ ደረስ በእጥፍ አሳድጎ 70 በመቶ ለማደረስ አቅዷል።












