የትግራዩ ግጭት 5ሺህ ሕጻናትን ከወላጆቻቸው ለይቷል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት በትግራዩ ግጭት ምክንያት ወደ 5ሺህ የሚጠጉ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ጋር ተለያይተዋል አለ።
ሕጻናት አድን ድርጅቱ እንዳለው ከወላጆቻቸው የተለዩ ሕጻናት በስደተኛ እና ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።
ሴቭ ዘ ቺልድረን እንደሚለው ከወላጆቻቸው የተለዩት ሕጻናት ለረሃብ፣ ለአካላዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች ተጋላጭ ናቸው።
ድርጅቱ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ለበርካታ የክልሉ ስፍራዎች እርዳታ ማቅረብ ባለመቻላቸው፤ ሕጻናቱ ያለማንም ድጋፍ እራሳቸውን ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ ብሏል።
ከስድስት ወራት በላይ በቆየው የትግራይ ጦርነት ከ1.7 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግጭቱ በክልሉ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ሲል ያስጠነቅቃል።
ተመድ ሕጻናት፣ የሚያጠቡ እና ነብሰ ጡር እናቶች ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት እያጋጠማቸው ስለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ ይላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የአፍሪካና የተቀረው ዓለም መሪዎች በትግራይ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድምፃቸውን የበለጠ እንዲያሰሙ ጥሪ አቅርቧል።
ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ለስድስት ወራት በዘለቀው የትግራይ ጦርነት በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብሏል።
አምነስቲ፤ 'ኦፕን ሶርስ' የተሰኘ የምርመራ መንገድ እንዲሁም የሳተላይት ምስሎች ትንተና እና የቪድዮ ምስሎች ማስረጃዎችን በመጠቀም የተለያዩ ጥሰቶችን እንደመዘገበ በመግለጫው አሳውቋል።












