በሌጎስ ብቻ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከመላው አፍሪካ በላይ ይሆናል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በናይጄሪያ ትልቋ የንግድ ከተማ ሌጎስ የተካሄደ ጥናት 4 ሚሊዮን የከተማዋ ነዋሪዎች በኮሮናቫይረስ ሳይያዙ እንዳልቀረ ጠቆመ።
ይህ አሃዝ በመላው አፍሪካ በቫይረሱ እንደተያዙ በይፋ ከተነገረው ሰዎች ቁጥር በላይ ነው።
ናይጄሪያ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 153 ሺህ ነው ያለች ሲሆን፤ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥርን ደግሞ አንድሺህ 862 ነው ብላለች።
በአራት የናጄሪያ ግዛቶች ላይ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላት አፍሪካዊቷ አገር የቫይረሱ ስርጭት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማወቅ ያለመ ነበር። መስከረም እና ጥቅምት ወራት ላይ የተካሄደው ጥናት ያስመለከተው ውጤት በርካቶችን ያስገረመ ሆኗል።
በጥናቱ ውጤት መሠረት ከአራቱ ናሙና ከተሰበሰበባቸው ግዛቶች በሦስቱ ግዛቶች ከአምስት ሰዎች አንዱ በቫይረሱ ተይዞ እንደነበረ 'የአንቲቦዲ' ምርመራ ውጤቶች አስመልክተዋል። በአራተኛዋ ጎምቤ ግዛት ደግሞ ከ10 ሰዎች አንዱ በቫይረሱ ተይዞ ነበር ተብሏል።
ጥናቱ እንዳሳያው በቫይረሱ የተያዙት አብዛኛዎቹ ወንዶች ሲሆኑ የከተማ ነዋሪዎች ደግሞ የበለጠ ተጋለጭ እንደሆኑ ጥናቱ አስመልክቷል።
የናጄሪያ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል እና የሕክምና ምርምር ተቋም ያካሄዱት የዳሰሳ ጥናት 186 ሚሊዮን የናይጄሪያ ዜጎች ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸውን አሳይቷል።
የናይጄሪያ ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት 206 ሚሊዮን እንደሆነ ይገመታል።
"በአራቱ ግዛቶች ከሚኖረው ጠቅላላ ሕዝብ 81 በመቶ የሚሆነው አሁንም ለቫይረሱ ተጋላጭ ነው። ይህም ክትባት መሰጠትን እጅግ ወሳኝ ያደርገዋል" ሲሉ የናይጄሪያ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ቺኬዋ ኢሄንከዌዙ ተናግረዋል።

ናይጄሪያ በቅርቡ ኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ያመረቱትን ክትባት ለዜጎቿ ለመስጠት ወስናለች።
ባለሙያዎች በቫይረሱ ማን የት እና መቼ እንደተያዘ መለየት እንዲሁም በቫይረሱ ህይወታቸውን ያለፈ እና ያገገሙ ሰዎችን በትክክል መለየት ግብዓቶችን በትክክል ለመመደብ ያስችላል ይላሉ።
በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎችን አሃዝ በተመለከተ መንግሥታት የሰጧቸው ቁጥሮች አነስተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው በአህጉሪቱ የሚከናወኑት የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ነው።












