ፈረንሳይ አዛውንት ዜጎቼን አስትራዜኒካ ክትባትን አልከትብም አለች

Vaccine center

የፎቶው ባለመብት, EPA

የፈረንሳይ የጤና ሚኒስቴር አስትራዜኔካ የኮቪድ ክትባትን በዕድሜ ለገፉ ዜጎች መሰጠት የለበትም ሲል ወሰነ።

ምክንያቱ ደግሞ ክትባቱ በአዛውንቶች ዘንድ የሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳትን በተመለከተ አጥጋቢ ምርምር አልተደረገም፣ የተደረገው ምርምር ውጤትን የሚያሳይ መረጃም ገና አልደረሰንም በሚል ነው።

ክትባቱ አይሰጣቸውም የተባሉት ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑት ዜጎች ነው።

የአውሮጳ ኅብረት የመድኃኒት ቁጥጥር ክፍል ኦክስፎርድ አስትራዜኒካ ክትባት ለሁሉም አዋቂዎች መሰጠት ይችላል ብሎ ያጸደቀ ሲሆን ነገር ግን አባል አገራት የፈለጉትን የዕድሜ ወሰን ሊያስቀምጡ ይችላሉ ሲል መብት ሰጥቷል።

ከፈረንሳይ ቀደም ብሎ ጀርመንና ኦስትሪያ ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው መዘገቡ ይታወሳል።

አገራቱ ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች ክትባቱን ለመስጠት የሰጉት በቂ የምርምር መረጃ ወይም ዳታ አልቀረበም በሚል ነው።

የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው በክትባቱ ዙርያ ሙሉ ዳታ በሚቀጥለው ሳምንት ይደርሳል። እስከዚያ ግን ከ65 ዓመት በታች ላሉት ብቻ ክትባት እንሰጣለን ብሏል።

ክትባቱን በቅድሚያ የሚያገኙት ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 65 የሆኑትና የሥራ ባህሪያቸው ለተህዋሲው ተጋላጭ ያደረጋቸው ዜጎች ናቸው።

በፈረንሳይ እስከ አሁን 1.5 ሚሊዮን ዜጎች ክትባት ደርሷቸዋል። የፈረንሳይን ያህል ሕዝብ ያላት ታላቋ ብሪታኒያ 10 ሚሊዮን ሕዝቦቿን ከትባ ጨርሳለች።

ሆኖም የአውሮጳ ኅብረት ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ክሌመንት በሰጡት አስተያየት ታላቋ ብሪታኒያ ለዜጎች የሚሰጠውን ሁለት ጠብታ ለጊዜው አንድ አንድ በማደል ትልቅ አደጋን ጋብዘዋል ሲሉ በሬዲዮ አስተያየተ ሰጥተዋል።

ሳይንቲስቶች አንድ ሰው አንድ ጠብታን ወስዶ ሁለተኛውን ከሚጠብቅ ሁለቱን ጠብታ ቢወስድ ነው የተሻለው ነው የሚሉት ያሉት ሚኒስትሩ ዩኬ ግን አሻፈረኝ ብላለች ሲሉ ተችተዋል።

አስትራ ዜኒካ በሳምንታት ልዩነት 2 ጠብታዎችን መወጋትን የሚሻ የክትባት ዓይነት ነው።

የአውሮጳ ኅብረት አገራት ሚኒስትሮች ይህ ክትባት ለየትኛው ዕድሜ ላሉ ይሰጥ በሚለው እየተወዛገቡ ነው።

ጀርመን እና ኦስትሪያ ከ65 በታች ለሆኑት ብቻ ለመስጠት ሲወስኑ ቤልጂየም ግን ከ55 በታች ብቻ ነው የምሰጠው ብላለች። ጣሊያንም በተመሳሳይ ከ55 ዕድሜ በታች ብቻ ላሉት ክትባት ለማደል ወስናለች።

ስዊድንና ፖላንድም ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።