ኮሮናቫይረስ፡በሞዛምቢክ በርካታ ተማሪዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል ተባለ

በደቡባዊቷ አፍሪካዊት አገር ሞዛምቢክ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል ተባለ።

በመዲናዋ ማፑቶ አርባ ተማሪዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የትምህርት ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

የተማሪዎቹ በኮቪድ-19 መያዝ የታወቀው ባለፈው ሳምንት ቢሆንም ሁኔታው ግን ይፋ የተደረገው በትናንትናው እለት በትምህርት ቢሮ ዳይሬክተሩ ዲኦሊንዳ ኮሳ አማካኝነት ነው።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው አርባ ተማሪዎች መካከል 23ቱ ካሳ ዶ ጋያቶ የተባለ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ በቅርቡ የነበሩ በዓላትን ለመታደም ቤታቸው ደርሰው የተመለሱም መሆናቸው ተገልጿል።

የተወሰኑት ተማሪዎች በኮሮና ህሙማን ማዕከል እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ተደርገዋል።

የማፑቶ ግዛት አስተዳዳሪ ጁሊዮ ፓሩኬ እንዳሉት ትምህርት ቤቶች የማህበረሰባዊ ጤናን በጥብቅ እንዲከታተሉና የወረርሽኙንም ስርጭት ለመግታት አጥብቀው እንዲሰሩ ተማፅነዋል።

አስተዳዳሪው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጭምብል ማጥለቅ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና በተደጋጋሚ እጅን መታጠብ አስገዳጅ አንደሆነም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።