ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦስትሪያ ትምህርት ቤት ውስጥ ሂጃብ ማድረግ የሚከለክለውን ሕግ ሰረዘች
የኦስትሪያ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሂጃብን ጨምሮ የተለያዩ ሐይማኖት መገለጫዎችን ማድረግ የሚከለክለውን ሕግ ሰረዘ።
ሕጉ የሐይማኖት ነፃነትን የሚጋፋ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
ሕጉ የተላለፈው ወግ አጥባቂው 'ፒፕልስ ፓርቲ' ከግራ ዘመሙ 'ፍሪደም ፓርቲ' ጋር ጥምር መንግሥት መስርቶ በነበረበት ወቅት ነው።
ፍርድ ቤቱ ሕጉ ሴት ሙስሊሞችን አግላይ እንደሆነ ተናግሯል።
መንግሥት ሕጉን ሲያወጣ ሙስሊም ተማሪዎች በክፍል ጓደኞቻቸው ጫና እንዳይድርባቸው ለመጠበቅ ነው ቢልም፤ ፍርድ ቤቱ ግን "ሕጉ ወንጀለኛ አድርጎ ያስቀመጠው ትክክለኛውን ሰው አይደለም" ብሏል።
ፍርድ ቤቱ አክሎም፤ መንግሥት ሙስሊም ተማሪዎችን መከላከል ከፈለገ ሐይማኖት እና ፆታን መሠረት አድርገው መድልዎ የሚያደርሱ ሰዎችን የሚቀጣ ሕግ ነው ማውጣት ያለበት ብሏል።
ሕጉ ተግባራዊ የተደረገው አምና ነበር። ሂጃብ ማድረግ ክልክል ነው ብሎ በግልጽ ባያስቀምጥም፤ "እስከ 10 ዓመታቸው የሆኑ ልጆች ራስ ላይ የሚጠመጠሙ ሐይማኖታዊ ልብሶችን ማድረግ አይችሉም" ይላል።
የሲክ እና የአይሁድ እምነት ተከታይ ልጆችን ሕጉ እንደማያካትት መንግሥት ተናግሯል። ስለዚህም ሕጉ ሂጃብ ላይ ያነጣጠ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
የፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት ክሪስቶፍ ግራቤንዋርተር "ሕጉ ክልከላ የጣለው ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ነው። ይህ ሕግ ከሌሎች ተማሪዎች ነጥሎ ያገላቸዋል" ብለዋል።
የትምህርት ሚንስትር ሄንዝ ፋስማን "ሴቶች ያለ ጫና በትምህርት ሥርዓቱ ማለፍ አለመቻላቸው ያሳዝናል" ብለዋል።
የኦስትሪያ የሙስሊም ማኅበረሰብ ተቋም ሕጉ መሻሩን በደስታ ተቀብሎታል።
"ሴቶችን እኩል እድል ማግኘታቸውን ማረጋገጥ እና በራሳቸው የሚወስኑትን መቀበል የሚቻለው ክልከላ በመጣል አይደለም" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ሕጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲረቅ፤ መራሔ መንግሥት ሰባስሽን ከርዝ "ሕጉ የኦስትሪያ ማኅበረሰብ ውስጥ ተነጥሎ የሚወጣ ማኅበርን ያስወግዳል" ብለው ነበር።
የፍሪደም ፓርቲ ምክትል መራሔ መንግሥት ሄንዝ ክርስትን ስትራቼ፤ መንግሥት ታዳጊ ሴቶችን "ከፖለቲካዊ እስልምና" ለመጠበቅ እየሞከረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚያም ሕጉ እአአ 2019 ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ተድርጓል።
አሁን ላይ ፒፕልስ ፓርቲ ከግሪን ፓርቲ ጋር ተጣምሯል። ሂጃብ የሚከለከለውን ሕግ እስከ 14 ዓመት በደረሱ ታዳጊዎች ላይ ተግባራዊ የማድረግ እቅድ ነበረ።