ኦባማ ቭላድሚር ፑቲንን እና ሌሎችም የዓለም መሪዎችን እንዴት ይገልጿቸዋል?

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የጻፉት 'ኤ ፕሮሚስድ ላንድ' ለገበያ በቀረበ በ24 ሰዓት ውስጥ በአሜሪካ እና በካናዳ ወደ 890,000 ቅጂ ተሸጧል።

በፕሬዘዳንቶች ከተጻፉ ግለ ታሪኮች ብዙ ቅጂ በመሸጥ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝም ይጠበቃል።

ኦባማ፤ ቭላድሚር ፑቲን፣ አንግላ መርኬል እና ሌሎችም የዓለም መሪዎችን እንዴት እንደሚያዩዋቸው በመጽሐፉ አካተዋል።

ቭላድሚር ፑቲን

ኦባማ ወጣት ሳሉ በቺካጎ የገጠሟቸውን ፖለቲከኞች በመጥቀስ፤ የሩስያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን "እነዛን ሰዎች ያስታውሰኛል" ይላሉ።

"ኒውክሌር እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድምጽ በድምጽ መሻር ሥልጣን ያለው የግዛት መሪ" ሲሉ ይገልጿቸዋል።

ቺካጎ ውስጥ የነበረ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርን አስታውሰው "ጠንካራ፣ ለስላሳ ያልሆነ፣ ከጠባብ ተሞክሮው የማይወጣ አመራርን ያስታውሰኛል። በተጨማሪም ፑቲን ጉቦ መስጠት፣ ማጭበርበር፣ አንዳንዴም ሰውን ማንገላታት ችግር እንደሌለው የሚያስበውን ሰው ያስታውሰኛል" ብለዋል።

ዴቪድ ካሜሩን

የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ወግ አጥባቂ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንን "በራስ መተማመኑ ሕይወት ብዙም እንዳልከበደው ያሳያል" ሲሉ ይገልጿቸዋል።

ከካሜሩን ጋር በቀላሉ መግባባት እንደቻሉ ኦባማ ይናገራሉ። የምጣኔ ሀብት ፖሊሲን በተመለከተ ባይስማሙም "እንደ ግለሰብ ግን ደስ ብሎኝ ነበር" ይላሉ።

"ካሜሩን የነፃ ገበያ ደጋፊ ነው። ለመራጮች ቃል ከሚገባው መካከል ለውጥ በማካሄድ ንግድን የማስፋፋት ውጤት የሚያመጡ እርምጃዎች ይገኙበታል። ሆኖም ግን እንደተገመተው የእንግሊዝ ምጣኔ ሀብት ውድቀት ገጠመው" ሲሉ ኦባማ ጽፈዋል።

ኒኮላስ ሳርኮዚ

ኦባማ፤ የቀድሞውን የፈረንሳይ ፕሬዘዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ "ስሜታዊ። ከቶሊስ-ላውትሬ ሥዕል የወጣ የሚመስል ሰው" ሲሉ ነው በመጽሐፋቸው የገለጹት።

ከሳርኮዚ ጋር ያደረጉት ንግግር አስደሳች እንደነበር ያስታውሳሉ። በተደጋጋሚ እጃቸውን ያወናጭፉ እንደነበር ገልጸውም "አስተርጓሚው የሱን የሰውነት እንቅስቃሴና ድምጸት ያስመስላል" ብለዋል።

ወሬያቸው እርስ በእርስ ከመሞጋገስ ወደላቀ የሐሳብ ልውውጥ ማደጉን፣ ዋነኛ ግባቸው የውይይቱ ማዕከል መሆንና እውቅና ማግኘት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

አንግላ መርክል

የጀርመኗ መራሔተ መንግሥት "በአቋም የጸናች፣ ሀቀኛ፣ ባለ ምጡቅ አእምሮ እና ቀና" በሚል ነው በኦባማ የተገለጹት።

መጀመሪያ ላይ መርክል ኦባማን በሙሉ ልብ ለመቀበል ተቸግረው ነበር።

ኦባማ መጽሐፋቸው ላይ እንዳስነበቡት ይህንን የመርክል ባህሪ እንግዳ ሆኖ አላገኙትም።

"አልተቀየምኳትም። እንደ ጀርመናዊት መሪ ከማንኛውም የማኅበረሰቡ አካል ጋር መዛመድ ወደሚችል ንግግር እንደምትሻገር ተረድቻለሁ" ይላሉ።

ፕ ታይፕ ኤርዶዋን

የቱርኩ መሪ ኤርዶዋን፤ ከኦባማ ጋር ወዳጅ እንደነበሩና የኦባማን ፍላጎት እንዳሟሉ ይናገራሉ።

"ሲናገሩ ድምጻቸው ኃይል አለው። በኔ እይታ ዴሞክራሲን የማስፈን ተነሳሽነታቸው የሚዘልቀው ሂደቱ ሥልጣናቸውን የማይነካ ከሆነ ብቻ ነው" ብለዋል።

ማንሞሀን ሲንግ

"ብልህ፣ አሳቢ፣ እውነተኛ" ሱሉ ነው ስለቀድሞው የሕንድ ጠቅላይ ሚንስተር የጻፉት።

የሕንድ የምጣኔ ሀብት እድገት ቀማሪ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም "የሕዝቡን ቀልብ የሚገዛም ስሜታቸውን በመኮርኮር ሳይሆን ሕይወታቸውን በመለወጥ ነው። ሙስና ባለመፈጸም ስማቸውን አስከብረዋል" ይላሉ።

ቫክላቭ ክላውስ

ከአብዮቱ በኋላ የቼክ ሪፐብሊክ የመጀመሪያ ፕሬዘዳንት የነበሩት ቫክላቭ ሀቫልን የሚያደንቁት ኦባማ፤ ከምክትላቸው ቫክላቭ ክላውስ ጋር ብዙም አልተጣጣሙም ነበር።

አክራሪ ቀኝ ዘመምነት በአውሮፓ የማንሰራራቱ ማሳያ እንደሆኑ በመጽሐፋቸው ገልጸዋል።

"2008 ላይ የተከሰተው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ብሔርተኛነትን አጠንክሯል። የአውሮፓ ጥምረት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ እና ስደተኞች ተቀባይነት እንዲያጡም ምክንያት ሆኗል" ሲሉ ኦባማ ጽፈዋል።

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ ዴሞክራሲ፣ አንድነት እና ነፃነት ይሰፍናል የሚለውን ተስፋ መሸርሸራቸውንም አያይዘው ጠቅሰዋል።