የፌደራል ፖሊስ 14 የውጪ አገራት ዜጎች የአደንዛዥ ዕፅ ሲያዘዋውሩ መያዙን ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Federal Police
የፌደራል ፖሊስ 13 ናይጄሪያውያንና አንድ ብራዚላዊት አደንዛዥ ዕጽ ሲያዘዋውሩ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ።
ግለሰቦቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉት በቦሌ ኣለም አቀፍ አውሮፕላን መሆኑ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።
የፌደራል ፖሊስ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 24 የአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለፀ ሲሆን 39 ኪሎ ግራም ኮኬይንና 36 ኪሎ ግራም የሚመዝን ካናቢስ (ዕፀ-ፋርስ) መያዙ ተገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት በትናንትናው እለት (ጥቅምት 9፣ 2013 ዓ.ም) በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ መነሻቸውን ላቲን አሜሪካ፣ ሳኦፖሎ ከተማ፣ መዳረሻቸውን ደግሞ የተለያዩ ሀገራት ለማድረግ በአውሮፕላን ሲጓዙ የነበሩት ተጠርጣሪዎችን እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ኮሚሽኑ ባሰራጨው ዜና አስታውቋል።
የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎቹ የያዝዋቸውን ዕጾች በውስጣዊና ውጫዊ የሻንጣ አካል ተደብቀው እንደነበር ተገልጿል።
በተጨማሪም በሆዳቸው በመዋጥ እንዲሁም የጡት መያዣና የተለያዩ የማዘዋወሪያ ዘዴዎችን ተጠቅመው ለማሳለፍ ሙከራ ማድረጋቸው በመረጃው ላይ ተመልክቷል።
ተጠርጣሪዎቹ ከ14 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ኮኬይን ይዘው ተገኝተዋል።








