ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወሲባዊ ጥቃት፡ ባንግላዲሽ ደፋሪዎችን በሞት ልትቀጣ ነው
ባንግላዲሽ በመድፈር የተከሰሱ ሰዎችን በሞት ልትቀጣ ነው። በአገሪቱ የተባባሰውን ወሲባዊ ጥቃት በመቃወም ለቀናት ሰልፍ ከተካሄደ በኋላ ነው የሞት ቅጣት በሕጉ እንዲካተት የተወሰነው።
የሕግ ሚንስትሩ አኒሹ ሐቅ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የፊታችን ማክሰኞ ፕሬዘዳንቱ ቅጣቱን በይፋ የሕጉ አካል ያደርጋሉ።
በቡድን አንዲት ሴት ላይ ጥቃት ሲፈጸም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መለቀቁን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ ተቃውሞ ነበር።
አንድ የመብት ተሟጋች ቡድን ባለፈው ዓመት 5,400 ሴቶች መደፈራቸውን መዝግቧል። ሆኖም ግን ለፍርድ የሚቀርቡት ደፋሪዎች እምብዛም አይደሉም።
ብዙ ሴቶች መገለል ይደርስብናል ብለው ስለሚሰጉ መደፈራቸውን ሪፖርት አያደርጉም።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨው ቪድዮ አስቆጥቷቸው ሰልፍ የወጡ ሰዎች፤ የፍትሕ ሥርዓቱ ጉዳዩን የሚያይበት መንገድ መለወጥ እንዳለበትና የፍርድ ሂደቱ ፈጣን መሆን እንደሚገባው አስረግጠዋል።
የባንግላዲሽ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምርመራ እንደሚያሳየው፤ በቪድዮው ላይ የታየችው ሴት በተደጋጋሚ ተደፍራለች።
ቪድዮው ከተሰራጨ በኋላ ስምንት ወንዶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ባለፈው ሳምንት በባንግላዲሽ ደቡባዊ ግዛት ሲልሄት በሚገኝ ሆቴል ውስጥ አንድ ሴት በቡድን ተደፍራለች። ይህን ተከትሎም የገዢው ፓርቲ የተማሪዎች ክንድ በርካታ አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ባንግላዲሽ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። "ደፋሪዎች ይሰቀሉ"፣ "ደፋሪዎች ይቅር አይባሉም" የሚሉና ሌሎችም ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው መፈክሮች በመዲናዋ ዳካ ተሰምተዋል።
ተቃውሞውን ተከትሎ መንግሥት ሕጉ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ወስኗል።