ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶ/ር ቴድሮስ እና ዘ ዊኬንድ በታይም መጽሔት የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እና ታዋቂው ዘፋኝ 'ዘ ዊኬንድ' በታይም መጽሔት የዓመቱ የዓለማችን 100 ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ።
ከኮሮናቫይረስ የዓለምን ሕዝብ ለመታደግ ከፊት መስመር ሆኖ ትግል የሚያደርገውን የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመሩት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ እና ከትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቤተሰብ የተገኘው ካናዳዊው ዘፋኝ አቤል ተስፋዬ በመድረክ መጠሪያው 'ዘዊኬንድ' በዝርዝሩ ውስጥ ይገኛሉ።
እውቁ ታይም መጽሔት በየዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው የሚላቸውን የ100 ሰዎች ስም ዝርዝርን ይዞ ይወጣል።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ የአገራት እና የድርጅት መሪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የእንቅስቃሴ መሪዎች፣ አርቲስቶች እና ስፖርተኞች እንዲሁም ጸሐፊዎች ይካተቱበታል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በታይም መጽሔት የ2020 ተጽእኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ሰዎች በእኩልነት የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ባበረከቱት አመራር ነው።
"አስቸጋሪ ወቅቶች ማንነታችን ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ኮቪድ-19 ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ወሳኝ ከስተት ነው። ልምድ ያካበቱት ተመራማሪው እና የሕብረተሰብ ጤና መሪው ዶ/ር ቴድሮስ ለኮቪድ-19 የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ካልጠበቅን ሁላችንም ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆንን ያውቃሉ" ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ለታይም የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ እንዲከታቱ ያጩት ናይጄሪያዊቷ ጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ ጽፈዋል።
ዓመቱ ለዶ/ር ቴድሮስ የፈተናና የስጋት ባቻ ሳይሆን ከፍተኛ እውቅናን የተጎናፈፉበት ነው። ከእነዚህም መካከል ትናንት የ2020 "ብሪጅ ሜከር አዋርድ" ሽልማታቸውን ከፈረንሳይ መቀበላቸው ይታወሳል።
በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት የአገራት መሪዎች መካከል የጀርመኗ መረሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል፣ የብራዚሉ ፕሬዝደንት ጄይል ቦልሶናሮ፣ የሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የዲሞክራት የፕሬዝደንት እጩ ጆ ባይደን፣ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ፣ የፓሪስ ከተማ ከንቲባ አን ሂዳልጎ፣ በአሜሪካ የዩናትድ አረብ ኤሜሬትስ አምባሳደር የሱፍ አል ኦታይባ ተጠቃሽ ናቸው።
ከ15 በላይ እውቅ የጥበብ ሰዎች የተዘረዙ ሲሆን ከትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቤተሰብ የተገኘው 'ዘ ዊኬንድ' አቤል ተስፋዬ ከዝርዝሩ አናት ላይ ተቀምጧል። ጥቁር አሜሪካውያኑ ተዋናያኖች ገብርኤላ ዩኒየን እና ቴይለር ፔሪ በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት [2019] የታይም መጽሔት 100 ተጽእኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተው እንደነበረ ይታወሳል።
ከፍተኛ ተከፋይዋ ሴት ስፖርተኛ የሆነችው ጃፓናዊቷ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቿ ናኦሚ ኦሳካ የታይም የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችላለች። ካረቢያን ውስጥ በምትገኘው ሄይቲ ከተወለዱት አባቷ እና ከጃፓናዊት እናቷ የተገኘችው ናኦሚ በቅርቡ የዩኤስ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ ውድድርን ማሸነፏ ይታወሳል።
የፎርሙላ ዋነ (Formula 1) ተወዳዳሪ የሆነው እንግሊዛዊው ሉዊስ ሃሚልተን በዝርዝሩ ውስጥ ተካቷል። ሉዊስ ሃሚልተን 'የብላክ ላይቭስ ማተር' እንቅስቃሴን በፎርሙላ ዋን ወድድሮች እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጉልቶ በማውጣት እንቅስቃሴው በርካቶች ጋር እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል።
የመብት ተሟጋቹ ናታን ሎው የዓመቱ ተጽአኖ ፈጣሪ ግለበሶች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል። የዴሞክራሲ መብቶች አቀንቃኙ ናታን ምንም እንኳ በስደት ከሆንግ ኮንግ እርቆ ቢገኝም፤ የቤይጂንግ መንግሥት የሆንግ ኮንግን የራስ ገዝ ነጻነት እምኖ እንዲቀበል ጥረት ያደርጋል።