የተቋረጠው የህዳሴ ግድብ ድርድር በመጪው ሳምንት ሊቀጥል እንደሚችል ተገለፀ

በአፍሪካ ህብረት ታዛቢነት እየተደረገ ያለው የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሶስትዮሽ የበይነ መረብ ድርድር የተቋረጠ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንትም ይቀጥላል ብላ ኢትዮጵያ እንደምትጠብቅ በዛሬው ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ አርብ ማለዳ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ በአሁኑ ወቅት ግብፅ እና ሱዳን ተቃውሞ ያነሱባቸው ኃሳቦች አዲስ እንዳልሆኑና ኢትዮጵያ የግድቡ ሙሌት ያለ ስምምነት አሁን ተፈፅሞ ተራዛሚ ጉዳዮች በሌላ ስምምነት መከናወናቸው እንዲቀጥል ትፈልጋለች ብለዋል።

ግብጽ ከምታነሳቸው ቅሬታዎች መካከል ኢትዮጵያ ግድቡን ሙሉ አቅም እየተጠቀመች ድርቅ ቢያጋጥም ችግሩ የሦስቱም አገራት ጉዳይ ነው የሚል አቋም ላይ መድረሷን ነው።

ወደፊት ድርቅ ቢያጋጥም ኢትዮጵያዊያንን ግምት ውስጥ ያስገባ የውሃ አጠቃቀም ማድረጓ አይቀርም የሚል ኃሳብን የሰነዘሩት አምባሳደሩ፣ ነገር ግን ከአሁኑ ሊኖረው የሚችለውን የውሃ መጠን ለመወሰን ትቸገራለች ሲሉ አክለዋል።

ከግድቡ ድርድር ታዛቢዎች መካከል አንደኛዋ ከሆነችው አሜሪካ ጋር ኢትዮጵያ ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲያብብ እንደምትፈልግ የተናገሩት ዲና ሆኖም ጫና የማሳደር ሙከራዎችም አንቀበልም ሲሉ ተናግረዋል።

"ከአሜሪካ ጋር ያለን ግንኙነት ታሪካዊ ነው፤ ረጅምም ግንኙነት ነው፤ በርካታ ነገሮችን አብረን ሰርተናል" ያሉት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት "እንንከባከበዋለን፤ እንዲያድግ ነው የምንፈልገው፤ እንዲበላሽ አንፈልግም።"

ኢትዮጵያ ዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረውንም ድርድር ያቋረጠችበት ምክንያት በግብጽ ፍላጎት ታዛቢ እንዲሆኑ የገቡት አሜሪካና የዓለም ባንክ ለግብጽ ከመወገን አልፈው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ላይ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል በማለት ኢትዮጵያ መውቀሷ የሚታወስ ነው።

አሜሪካ፣ የዓለም ባንክ ከግብጽ ጎን ቆመው ነበር በተባለው በዚህ ድርድር ላይ ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብጽ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ እንደሆነም ተገልጾ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ የግብጽ ሃሳብ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብት እንዳይኖራት ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዲኖር የሚጠብቅ ነው በማለትም ተችታለች ።

በድርድሩ ላይ ግብፅ እና ሱዳን በተደጋጋሚ እየወጡ እየገቡ "ቢያሰለችም፣ [ድርድር] ተስፋ የሚቆረጥበት ጉዳይ አይደለም" ያሉት አምባሳደሩ በሚቀጥለው የሁለቱ አገራት ተደራዳሪዎች በጠየቁት መሰረት በጊዜያዊነት የተቋረጠው ድርድር ኢትዮጵያ ባቀረበችው የውኃ ሙሌት ደንብ ላይ ውይይት አድርገን እንመለስ በሚል ባሉት መሰረት ሰኞ እንደሚቀጥል እንጠብቃለን ሲሉ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በውሃ ሙሌቱ ላይ ያላትን ኃሳብ ብታቀርብም በተዛላቂ የውሃ ድርሻ እና አጠቃቀም ላይ ግን ሌላ ራሱን የቻለ ውይይት መደረግ ይገባዋል ብላ እንደምታምን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ግብፅ በኢትዮጵያ ዙርያ በሚገኙ አገራት ወታደራዊ የጦር መንደሮች ለማቋቋም እየጣረች ነው የሚሉ ዘገባዎች መሰራጨታቸውን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው አምባሳደር ዲና "ግብፅ እንደሉዐላዊ አገር ከፈለገችው አገር ጋር ግንኙነት መፍጠር ትችላለች፤ ከሶማሊላንድም፣ ከሶማሊያም፣ ከሱዳንም ጋር። እነርሱ የሚፈጠሩት ግንኙነት ግን በኢትዮጵያ ኪሳራ መሆን የለበትም። በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ፣ በኢትዮጵያ ነፃነት ላይ፣በኢትዮጵያ ደህንነት ላይ ያነጣጠረ መሆን የለበትም" ሲሉ መልሰዋል።

"ይህንን ለሶማሊላንድም አስረግጠን ነው የምንነግራቸው፤ ለደቡብ ሱዳንም ለተቀሩትም አገራት።" ሲሉ አጠቃልለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሊባኖሷ መዲና ቤይሩት በደረሰው ፍንዳታ የአንድ ኢትዮጵያዊ ሕይወት ሲያልፍ ሌሎች ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና ላይ እንደሚገኙ አምባሰደር ዲና ሙፍቲ አረጋግጠዋል።

በትናንትናው ዕለትም ቢቢሲ በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል የሆኑት አቶ ተመስገን ኡመርንም ባናገረበት ከህይወት ማለፉ በተጨማሪ ህክምና እየተከታተለች የነበረች ኢትዮጵያዊት በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ እንደምትገኝም ገልጸዋል።

በቤይሩት ውስጥ የሚኖሩ እና ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ህልውናቸው ላይ ስጋት የተጋረጠባቸው ኢትዮጵያዊያንን ለመታደግ የቆንስላ ፅህፈት ቤቱ ስራ እየሰራ መሆኑን ጨምረው የተናገሩት ዲና፣ በአሰሪዎች ደመወዝ ከመከልከል አንስቶ ጎዳና ላይ እስከመውጣት ድረስ ፈተናን እየተጋፈጡ ያሉ ስደተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በፍንዳታው በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የሟቾችም ቁጥር መቶን የተሻገረ ነው።