ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የህወሓት አቋምና የብልጽግና መልስ
የትግራይ ክልልን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የፌዴራል መንግሥትን የሚያስተዳድረው የብልፅግና ፓርቲ መካካል ያለው የቃላት ልውውት በመብረድ ላይ ያለ አይመስልም።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ድረስ ስብሰባ ካካሄደ በኋላ ባወጣው ዘለግ ያለ መግለጫ በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ ያለውን ፍላጎት ደግሞ በማስረገጥ፣ ፓርቲው የምርጫን ጉዳይ "አጀንዳ ለመፍጠር" ሊጠቀምበት እየሞከረ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አወሉ አብዲ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ምርጫ ማካሄድ የፌዴራል መንግሥት እንጂ የክልል መንግሥት ስልጣን አይደለም። የምርጫ ቦርድ ሙሉ ስልጣን ነው። ምርጫ ቦርድ ደግሞ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ዳሰሳ ጥናት አድርጎ" ለሚመለከተው አካል አቅርቦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ተቀባይነት አግኝቷል በማለት በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አወሉ ለቢቢሲ።
ህወሓት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ባወጣው መግለጫው "የፌደራል መንግሥትን ስልጣን በአምባገነናዊ አኳኋን" ተቆጣጥሯል ያለውን ገዥውን ፓርቲ የሕዝቦችን መብት እየደፈጠጠ ነው ሲል ከሶ ነበር።
ጨምሮም "ሕዝባችን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው እና የማንም ፈቃድ የማይጠይቅበት፤ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተግባር ለመተርጎም በክልላችን ምርጫ እንዲደረግ እና ይህንን ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች" እንዲቀጥሉ መወሰኑን አስታውቆ ነበር።
የአገሪቱ ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫ "የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ወደፊት የሚካሄድ ስለሆነ" ይላሉ አቶ አወሉ፤ "ከዚያ ውጭ እናደርጋለን የሚሉት ነገር ዞሮ ዞሮ ጨዋታ ነው የሚል አስተያየት ነው በእኛ በኩል ያለው።"
አቶ አወሉ የህወሓትን መግለጫ በጥቅሉ "የተለመደ ክስ" እና "መሰረት ቢስ ውንጀላ" ሲሉ አጣጥለውታል።
"በክልሏ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን አቅቷት፣ የሕዝቦችን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ሲቸግራት እና በአጠቃላይ እዚያ አካባቢ ያለውን የፖለቲካ ሥነ ምህዳር፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በኃይል በመገደብ [. . . ] ውዥንብር ውስጥ ገብታ ነገሮች ሲዞሩባት ብልፅግና ፓርቲን መክሰስ ነው የያዘችው" ሲሉ በስልክ ለቢቢሲ በሰጡት አጭር ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።
ህወሓት ገዥውን የብልፅግና ፓርቲን ሕገ መንግስትን ጥሷል፣ ገደብ የለሽ የስልጣን ጥም አለው እና "ግለገል አምባገነን" ሆኗል ሲል በመግለጫው ላይ ከሷል።
አቶ አወሉ በበኩላቸው ህወሓትን "የተሸናፊነት አመለካከት" ተጠናውቶታል በማለት ክሱን ያጣጥላሉ ሲሆን ፓርቲያቸው ከህወሓት በኩል የተሰነዘረበት ነቀፌታ ብዙም እንደማያሳስበው ይተናግረዋል።
በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው አጠቃላይ ምርጫ በኮሮናቫይረስ መከሰት ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በአገሪቱ ምክር ቤት መወሰኑ ይታወሳል።
የትግራይ ገዢ ፓርቲ ህወሓት ግን "አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ" ምርጫውን በክልሉ ውስጥ እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ አሳውቋል።
ቢሆንም ግን የምርጫውን ሂደት በምን መልኩና በማን የበላይ ተቆጣጣሪነት እንደሚካሄድ እንዲሁም መቼ እንደሚሆን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።