ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአቶ በረከት እና የአቶ ታደሠ ጠበቃ ይግባኝ እንጠይቃለን አሉ
የአቶ በረከት ስምኦን ባለቤት ወ/ሮ አሲ ፈንቴ፤ በባለቤታቸው እና በአቶ ታደሰ ካሣ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እውነቱን ለሚያውቅ የሚያሳዝን እና የማይገባ ነው አሉ።
የሁለቱን ተከሳሾች ጉዳይ ሲመለከት የነበረው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትናንትናው [አርብ] ዕለት የእስር ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነው የአቶ በረከት ስምኦን ባለቤት በብይኑ ማዘናቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት።
"እንዲህ አይነቱ ፍርድ አይገባቸውም። በጣም ያሳዝናል። የፍርድ ሂደቱን ከመጀመሪያው ቀድሞ ለተመለከተው የሚደንቅ ነገር አይደለም" ያሉት ወ/ሮ አሲ፤ የፍርድ ሂደቱ ብዙ መሰናክሎች የነበሩበት እና በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙበት ነበር ብለዋል።
"በፍርድ ቤት ውስጥ ጩኸት እና ጫጫታ በሚሰማበት ሁኔታ፣ እነ በረከት ሲገቡ እና ሲወጡ እየተሰደቡ፣ ያ ሁሉ የፍትህ እና የጸጥታ አካላት ባሉበት ቦታ በማስፈራሪያ እና በስጋት ተውጠን የነበረውን የፍርድ ሂደት ስናስብ ይህ አይነት ውሳኔ ቢወሰን ምንም የሚገርም አይደለም" ብለዋል።
ወ/ሮ አሲ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ባለቤታቸው አቶ በረከትን ካገኙ ከአንድ ወር በላይ እንዳለፋቸው ገልጸው፤ "ከፍርዱ ውሳኔ በኋላ በርቀት ነው የተያየነው" ብለዋል።
አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ገምተው ነበር ወይ ተብለው የተጠየቁት ወ/ሮ አሲ፤ "በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ግምት እንዳላቸው አናውቅም። በረከት ግን ምንም መጥፎ ቢሆኑ እንዲህ ይጨክናሉ ብሎ አስቦ አያውቅም'' ብለዋል።
"በረከት አያውቃቸውም። 27 ዓመት ሙሉ አብሮ ቆይቶ አያውቃቸውም። በእኔ ግምት እንዲህ አይነት ፍርድ ይተላለፍብኛል ብሎ አልገመተም" ብለዋል።
የአቶ በረከት ስምኦን እና የአቶ ታደሠ ካሣ ጠበቃ የሆኑት ህይወት ሊላይ በበኩላቸው ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።
"በተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔም ሆነ በቅጣት ውሳኔው ላይ ይግባኝ እንጠይቃለን። ምክንያቱም ብዙ የመከላከያ ማስረጃ አቅርበን እራሳችንን ተከላክለናል ብለን ስለምናስብ በአቶ በረከትም ሆነ በአቶ ታደሠ ላይ በተሰጠው ብይን ይግባኝ እንጠይቃለን" ብለዋል።
"ይግባኙ ውድቅ ይሆናል የሚል እምነት የለንም። ምክንያቱም ያቃረብናቸውን ማስረጃዎችን ተመልክቶ ሰሚው ችሎቱ ውሳኔውን ሊያሻሽልላቸው ይችላል የሚል ሙሉ እምነት አለን። እንደውም ነጻ በሚል ያሰናብተናል ብለን ነው የምናምነው" ብለዋል ጠበቃ ህይወት።
ይሁን ባይሆን ግን የፍርዱ ተፈጻሚነት ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋር እንደሚጠይቁ ጠበቃዋ ተናግረዋል። "ቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባ ባሉበት ሁኔታ ባህር ዳር ታስረው ይቆዩ የሚባልበት ሁኔታ ተገቢ አይደለም" ብለዋል።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት በተለያዩ የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ በነበሩት በአቶ በረከት ስምኦን ላይ ስድስት ዓመት እስርና የ10 ሺህ ብር ቅጣት የጣለ ሲሆን በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ደግሞ የስምንት ዓመት እስርና የ15 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።