በቲቪ የምናያቸው ቭላድሚር ፑቲን እውነተኛው ናቸው ወይስ ቅጂ?

ፑቲን ናቸው ወይስ ቅጂያቸው?

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, እኒህ ሰው ፑቲን ናቸው ወይስ ቅጂያቸው?

ቅጂ ለካሴት ብቻ አይደለም። የሰውም ቅጂ አለው። በተለይ ራሺያን በስለላና በሰው ቅጂ ማን ያህላታል?

የመላምት ፖለቲከኞች ከሰሞኑ አንድ ጉዳይ ላይ እየተወዛገቡ ነው። ዘወትር በቲቪ የምናያቸው ሰውዬ "ቅጂው ፑቲን እንጂ ዋናው ፒቱን ስለመሆናቸው እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል?" እያሉ ነው።

ይህንኑ ጥያቄ ለራሳቸው ለፑቲን አንድ ጋዜጠኛ ከሰሞኑ አቅርቦላቸው ነበር። (ለየትኛው ፑቲን? አትበሉንና)

ፑቲን ያቺን አጮልቀው የሚፈግጓትን ፈገግታ አስቀድመው እንዲህ መለሱ። "እርግጥ ነው ቅጂው ይዘጋጅልህ ተብዬ በደኅንነት መሥሪያ ቤቴ በኩል በተደጋጋሚ ተጠይቂያለሁ። እኔ ግን ሐሳቡን ውድቅ አድርጌዋለሁ።"

ፑቲን ጨምረው እንዳብራሩት ሐሳቡ መጀመርያ የቀረበላቸው በፈረንጆቹ በ2000 ዓ.ም ነበር። ያን ጊዜ ራሺያ ከተገንጣዮቹ ቺቺንያዎች ጋር ብርቱ ጦርነት ውስጥ ነበረች።

የ67 ዓመቱ ፑቲን የቀድሞ የኬጂቢ ባልደረባ ነበሩ። በርካታ ምሥጢሮችን ከአካባቢው አገራት እየቃረሙ ኬጂቢን ያጠግቡት ነበር።

ለዓመታት ታዲያ በርካታ የሴራ ፖለቲከኞች ቪላድሚር ፑቲን ከአንድም ሁለት ሦስት ቅጂዎች አሏቸው ሲሉ በየድረ ገጹ ይሟገቱ ነበር።

ይህንን ስሱ ጥያቄ ለፑቲን ደፈር ብሎ ያቀረበላቸው ጋዜጠኛ አንድሬ ቫንድንኮ ይባላል። ታስ ለሚባል የራሺያ ዜና አገልግሎት ነው የሚሰራው።

ጥያቄውን ሲያቀርብ እንዲህ ብሎ ጀመረ "በኢንተርኔት የፍለጋ ቁልፍ ተዘውትረው የሚጻፉት "ፑቲን እና የፑቲን ቅጂ የሚሉ ሐረጎች ናቸው። እርስዎ የትኛው ኖት?"

እኚህስ ቢሆኑ?

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY

የምስሉ መግለጫ, ፑቲን ክሪሚያ በተደረገ የሞተርሳይክል ውድድር ላይ ተገኝተው ከአድናቂዎቻቸው ጋር ፎቶ ሲነሱ

በምላሹ ፑቲን እኔ ሐቀኛው ፑቲን ነኝ አሉ። አስፈላጊ ሲሆን ቅጂ እንደሚጠቀሙ ግን በይፋ አስተባብለዋል ማለት አይቻልም።

የቅጂው ሐሳብ በ1999 ጀምሮ ተደጋግሞ እንደሚነሳም ለጋዜጠኛው ነግረውታል።

ይህ በ2007 በፈረንጆች ቭላድሚር ፑቲን በሞንጎሊያ ድንበር አካባቢ የተነሱት ፎቶ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY

የምስሉ መግለጫ, ይህ በ2007 በፈረንጆች ቭላድሚር ፑቲን በሞንጎሊያ ድንበር አካባቢ የተነሱት ፎቶ ነው

ቭላድሚር ፑቲን ከአራት ዓመት በኋላ ሥልጣናቸውን ይለቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። የቅጂው ወሬ ቢያንስ በሐሳብ ደረጃ ያን ጊዜ ያበቃል። ነገር ግን ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ወይም በሌላ ሁኔታ ያቺን አገር ዳግም እንደሚዘውሯት ይጠበቃል።

ከጆሴፍ ስታሊን ወዲህ በዚያች አገር ለረዥም ዘመን ሥልጣን ላይ ወጥቶ አልወርድ ያለ የለም፤ ከፑቲን በስተቀር። አሁን ፑቲን በሥልጣን ላይ 20 ዓመት ሆኗቸዋል።

እርሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ በአሜሪካ ፕሬዝዳንቱ ቢል ክሊንተን ነበሩ። ፑቲን ከክሬምሊን ሳይወጡ 3 የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ዋይት ሃውስ ገብተው ወጥተዋል። 5 የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትሮች "ዳውኒንግ ነምበር-ቴን" [የጠቅላይ ሚኒስትሮቹ ጽህፈት ቤት] ገብተው ወጥተዋል።

ለዚህ ሁሉ ዘመን ክሬምሊን የነበሩት ፑቲን ግን ቅጂው ይሆኑ ወይስ ሁነኛው?