በናይጄሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ተገኘ

በአየር መንገድ የሚገኝ የሙቀት መለኪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ናይጄሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያውን ሰው ሪፖርት አደረገች።

ታማሚው ጣሊያናዊ ዜግነት ያለው ሲሆን ናይጄሪያ ውስጥ እንደሚሰራና ከሶስት ቀን በፊት( ፌብሪዋሪ 25) ከሚላን ወደ ሌጎስ መምጣቱ ተነግሯል።

የናይጄሪያ ጤና ጥበቃ ባለሰልጣናት ግለሰቡ ጤንነቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው፣ ሌጎስ በሚገኝ የሕክምና ተቋም ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የናይጄሪያ መንግሥት የብሄራዊ ድንገተኛ ጊዜ እቅድ አውጥቶ አሁን ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራው በመግባት የመከላከል ሥራውን መስራት መጀመሩን ተናግረዋል።

ከታማሚው ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉት በአጠቃላይ መለየት መጀመራቸውን ባለሰልጣናቱ ፀጨምረው አስረድተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወሳኝ ነጥብ ላይ መድረሱን በመግለጽ አገራት አስፈላጊውን የመከላከል እርምጃ ሁሉ እንዲወስዱ አሳስቧል።

ከቻይና ውጪ በአሁን ወቅት ኢራንና ጣሊያን የወረርሽኙ መገኛ ማዕከል ሆነዋል።

በኢራን ከፍተኛ ባለሰልጣናት ሳይቀር በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰውም ሞቷል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በሚገኙ ከ50 በላይ ሀገራት 80 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ይታወቃል።

እስካሁን ድረስ ከቻይና ውጪ 60 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በቻይና በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል።

በአፍሪካ ከናይጄሪያ ውጪ በአልጄሪያ እንዲሁም ግብጽ በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱ ይታወሳል።