የጀነራሉ ጦር የመንገደኞች አውሮፕላንን ኢላማ አደርጋለሁ ሲል አስፈራራ

ሊቢያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጀነራል ካሊፋ ሃፍታር የሚመራው ጦር የትሪፖሊን አየር ማረፊያ የሚጠቀሙ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ኢላማ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

የጦሩ ቃል አቀባይ በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ የሚየያርፉ የጦርም ሆነ የመንገደኞች አውሮፕላኖች መትተው ከመጣላቸው በፊት የመጨረሻ ያሉትን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ሰዓት በሊቢያ ሁለት ዋነኛ ተቀናቃኝ ኃይሎች ይገኛሉ። በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው በጠቅላይ ሚንስትር ፋዬዝ አል-ሴራጅ የሚመራው መንግሥት እና በጀነራል ካሊፋ ሃፍታር የሚመራው አማጺ ኃይል ናቸው።

በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው መንግሥት ትሪፖሊን ተቆጣጥሮ ይገኛል።

ታዲያ ከሳምንታት በፊት በተባበሩት መንግስታት እውቅና የተሰጠውን መንግሥት ለመደገፍ ቱርክ ወታድሮቿን ወደ ሊቢያ መላኳ የጀነራል ሃፍታር ጦርን አበሳጭቷል።

የጦሩ ቃል አቀባይ ቱርክ የትሪፖሊን አየር ማረፊያ የጦር ካምፕ በማድረግ ጥቃት እየሰነዘረችብን ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም 'ሚተጋ' የተባለው ከትሪፖሊ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኝ የነበረ አየር ማረፊያ ሮኬት ከተተኮሰበት በኋላ ሥራውን ለማቋረጥ ተገዷል።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ እውቅና ባለው መንግሥት እና በአማጺያኑ መካከል በነበረ ግጭት ቢያንስ 2 ሺህ ሊቢያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። 146 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

የጀነራል ሃፍታር ጦር ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ክፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

Presentational grey line

የሊቢያውን የእርስ በእርስ ጦርነት እና የሌሎች አገራት ጣልቃ ገብነት አሁንም የዓለም ትኩረትን እንደሳበ ነው።

ለመሆኑ ሊቢያውያን እዚህ አጣብቂኝውስብስ ነገር ውስጥ እንዴት ገቡ?

ልክ እንደ ሶሪያ ሁሉ፤ የሊቢያውያን ሰቆቃ የጀመረው የአረብ አብዮትን ተከትሎ ነው።

እ.አ.አ. 2011 ላይ በምዕራባውያኑ ኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት) ድጋፍ የረዥም ጊዜ የሊቢያ መሪ የነበሩት ሙዓመር ጋዳፊ ከሥልጣን ተባረሩ።

አምባገነኑ ሙዓመር ጋዳፊ በሊቢያውያን ለውጥ ናፋቂ ወጣቶች መንገድ ላይ ተጎተቱ፤ አይደፈሬው ተዋረዱ፤ ከዚያም በጥይት ተመትተው ተገደሉ። በሊቢያ አዲስ ለውጥ መጣ ተባለ።

ሊቢያውያን ግን አምባገነናዊ ሥርዓቱን በሕዝባዊ አብዮት ሲገረስሱት፤ ነጻነትን እና የተሻለ ሥርዓትን አልመው ነበር።

የሙዓመር ጋዳፊ ሞት ግን ሊቢያውያን የተመኙትን ለውጥ ሳይሆን፤ መግቢያ መውጫ ያሳጣቸውን የእርስ በእርስ ጦርነት ነው ያስከተለው።

የተባበሩት መንግሥታት በጠቅላይ ሚንስትር ሰርጀ የሚመራ መንግሥት መቀመጫውን በትሪፖሊ እንዲያደርግ አመቻቸ። ሁሉም በዚህ አልተስማማም፤ ጀነራል ሃፍታር ሥልጣን ፈለጉ።

ጀነራሉ በምስራቅ ሊቢያ በሚገኙ 'ቶበሩክ' እና 'ቤንጋዚ' ከተሞች መቀመጫቸውን አድርገው የራሳቸውን ጦር አደራጁ። ተጽእኖ ፈጣሪው ጀነራል፤ የሊቢያ ብሔራዊ ጦር የተሰኘ ኃይል አቋቁመው ካለ እኔ ለሊቢያ የሚፈይድ የለም፤ እኔ እንጂ ማንም "እስላማዊ አሸባሪዎችን" አያስወግድም አሉ።

ከዚያም በተመድ እውቅና ያለውን መንግሥት መውጋት ተያያዙት። ትሪፖሊን ለመቆጣጠር የጦር እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ 9 ወራት ተቆጠሩ።

ከጀነራሉ ጦር በተጨማሪ በሊቢያ ''ነጻ'' አውጪ ነን የሚሉ ኃይሎች በርካቶች ናቸው። ከየመሸጉበት እየወጡ፤ አንዱ አንዱን ይወጋል። በሊቢያ ''እስላማዊ መንግሥት'' መመሠረት አለበት ብለው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ብዙ ናቸው።

ተጽዕኖ ፈጣሪው ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ተጽዕኖ ፈጣሪው ጀነራል ካሊፋ ሃፍታር

የእጅ አዙር ጦርነት

በሊቢያ የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎች የውጪ ሃገራት ፍላጎትን ለማሳካት ነፍጥ አንግበዋል። በቀጠናው የሚገኙ ሃገራት በተለያየ አሰላለፍ የእጅ አዙር ጦርነት ወይም የውክልና ጦርነት ያካሂዳሉ።

ጀነራል ሃፍታር "እስላማዊ አሸባሪዎችን" እዋጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ጆርዳን ጽንፈኞች ከቀጠናው መጽዳት አለባቸው በማለት አጋርነታቸውን ከጀነራሉ ጋር አድርገዋል።

ጆርዳን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ከድጋፍም አልፈው የጀነራሉን ጦር አስታጥቀዋል፤ በተመድ እውቅና ባለው መንግሥት ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የአየር ላይ ድጋፍ ያደርጋሉ።

በግጭቱ ወቅት የተገደሉት ንጹሃን ዜጎች ለሞት ያበቃቸው የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ጦር መሳሪያ ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ይከሳል።

ከእነዚህ ሃገራት በተጨማሪ፤ ጎረቤት ሃገር ግብጽም የጀነራሉ አጋር ነች። አል ሲሲ ለጀነራል ሃፍታር ጦር የሎጂስቲክ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ።

ከአካባቢው ሃገራት በተጨማሪም ሞስኮ በሊቢያ እጇን እያስገባች እንደሆነ እየተነገረ ነው። ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በሩሲያ መንግሥት ተከፋይ የሆኑ የሌሎች ሃገራት ወታደሮች ከጀነራሉ ጎን ሆነው እየተዋጉ ይገኛሉ። የክሬምሊን መንግሥት ግን ቀጥተኛ ተሳትፎ የለኝም ይላል።

በሌላኛው በኩል ደግሞ ቱርክ የተመድ እውቅና የተሰጠውን መንግሥት ትደግፋለች። ከጥቂት ቀናት በፊትም ቱርክ ወደ ሊቢያ የትሪፖሊን መንግሥት ለመደገፍ ጦሯን ልካለች።

የቱርክ መንግሥት ጦሩን ወደ ሊቢያ የላከው "የሥልጠና እና የምክር አገልግሎት" ለመስጠት ታስቦ ነው ብሏል።

በሊቢያ መንግሥት ውስጥ የሚገኝ የቢቢሲ ውስጥ አዋቂ ግን በቱርክ በኩል ወደ ሊቢያ ከመጡ ወታደሮች መካከል በቱርክ የሚደገፉ የሶሪያ አማጺያን ይገኙበታል ብሏል።

በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ውስጥ ብዙውን ግዜ ተገልላ የምትገኘው ኳታር፤ በሊቢያ ጉዳይ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከቱርክ ጎን ተሰልፋለች።

line

የምዕራባውያን ሃገራት ፍላጎቶች

ሌላ የሊቢያ ጉዳይ ያገባኛል የምትለው ፈረንሳይ፤ የቱርክን አሰላለፍ ተቀላቅላለች። ፈረንሳይ የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለውን መንግሥት እደግፋለሁ ትበል እንጂ ልቧ ያለው ከጀነራሉ ጦር ጋር ነው ተብሎ ይታመናል።

የቀድሞ የሊቢያ ቅኝ ገዢ የሆነችው ጣሊያን፤ ፓሪስ ለጀነራሉ ጦር የምታደርገውን ድጋፍ አጥብቃ ካወገዘች በኋላ፤ ሮም ሁልጊዜም ተመድ እውቅና ለሰጠው መንግሥት ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች በሊቢያ በኩል አድርገው ሜዲትራኒያን ካቋረጡ በኋላ የመጀመሪያው መዳረሻቸው ጣሊያን ነች። በዚህም ጣሊያን የስደተኞችን ፍሰት ለማስቆም በሊቢያ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አለብኝ ባይ ነች።

ኃያሏ ሃገር አሜሪካም በሊቢያ በቀጥታ እጇን አስገብታለች። በደቡብ ምዕራብ ሊቢያ የሚገኙ የአይኤስ ሚሊሻዎች ላይም እርምጃ ትወስዳለች።

ይህ ሁሉ ሃገር በሊቢያ ጉዳይ እጁን የሚያስገባው ለምን ይሆን?

በሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት እጃቸውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያስገቡት ሃገራት ቁጥር ከፍተኛ ነው።

ለዚህም የመጀመሪያው ምክንያት ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት ሃገር ነች። በተፈጥሯዊ ጋዝ ገበያ ላይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሃገር መሆን ትችላለች።

ሌላኛው ምክንያት መዳረሻቸውን አውሮፓ ለማድረግ ከአፍሪካ የሚሰደዱ ወጣቶች መነሻቸውን የሚያደርጉት ከሊቢያ ነው። ሊቢያ ከ 2 ሺህ ኪ.ሜትር በላይ ከሜድትራኒያን ባህር ጋር እንደምትዋሰን እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

ከኢራቅ እና ሶሪያ ድል የተመታው ጽንፈኛው አይኤስ በሊቢያ በረሃዎች ላይ እግሩን እየከተተ መሆምኑ ተነግሯል። ይህ ለሊቢያ እና ጎረቤት አገሮች ብቻ ሳይሆን ለዓለም ደህንነት ስጋት ነው።