ቻይና ውስጥ በተከሰተው ቫይረስ በሁለት ቀናት 139 ሰዎች ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቻይና ባለሥልጣናት አዲስ እየተዛመት ባለው ቫይረስ በሁለት ቀናት ውስጥ 139 ሰዎች መያዛቸውን አሳወቁ።
ቫይረሱ ተከስቷል የተባለው ዉሃን በተሰኘችው ግዛት ሲሆን ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች የተገኙት ግን ከግዛቲቱ ውጭ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።
200 ሰዎች እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 3 ሰዎች በመተንፈሻ አካሉ ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። የዓለም ጤና ድርጅት ሰዎች በተመረመሩ ቁጥር አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር መጨመሩ አይቀርም እያለ ነው።
በሕክምናው አጠራር ኮሮናቫይረስ የተሰኘውና የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃው ቫይረስ መጀመሪያ የታየው በቻይናዋ ውሃን ግዛት ነው።
የእንግሊዝ የሕክምና ባለሙያዎች ግን ከሌሎች ባለሙያዎችና ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር ሆነን ባደረግነው ምርምር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መንግሥት ከሚለው የላቀ መሆኑን ደርሰንበታል ይላሉ።
ማዕከላዊ ቻይና የምትገኘው ዉሃን ግዛት ብቻ 136 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ ሶስቱም የቫይረሱ ሰለባዎች እዛው የሚገኙ ናቸው። ዉሃን ግዛት ዘመድ ጠይቆ የመጣ አንድ የሼንዘን ግዛት ነዋሪ የመጀመሪያ በሽታው ከታየበት ውጭ ያለ የቫይረሱ ተያዥ ሆኗል።
ዓለም አቀፉ የጤና ተቋም የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች በፍጥነት እንዲመረመሩ ጥሪ አቅርቧል።
የበሽታው መንስዔ የባሕር እንስሳት ሳይሆኑ እንዳልቀረ ግምት አለ። የቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው የመዛመት አቅምም ደካማ ነው ተብሏል። የቻይና ጤና ቢሮ 'በሽታውን መቆጣጠር የሚቻል ነው' ቢልም የበሽታው ምንጭ፣ የመዛመት አቅም እና መከላከያ መንገዶች ገና በውል አለመታወቁ ሁኔታዎችን ያከብዳቸዋል ተብሏል።
ቻይናዊያን በዚህ ሳምንት የሉናር አዲስ ዓመትን ያከብራሉ። ይህ ወቅት ደግሞ ብዙዎች ቤተሰብና ዘመድ ጥየቃ ከሥፍራ ሥፍራ የሚጓጓዙበት ነው።
ኮሮናቫይረስ የሚል የሕክምና ስያሜ ያለው በቫይረስ የሚከሰት በሽታ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ እንደ ጉንፋን ዓይነት የሆነ በሽታ ሲሆን ከበድ ሲል ግን ሊገድል እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በፈረንጆቹ 2002 ቻይና ውስጥ 'ሳርስ' የተሰኘ ስም የተሰጠው በሽታ 774 ሰዎችን መግደሉ አይዘነጋም። አዲሱ በሽታም ከሳርስ ጋር ተመሳሳይነት አለው እየተባለ ነው።













