ምዕራብ አውስትራሊያ የፍቃድ ሞትን ሕጋዊ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምዕራብ አውስትራሊያ በህክምና ባለሙያዎች የታገዘ የፍቃድ ሞትን ሕጋዊ በማድረግ ሁለተኛዋ የአውስትራሊያ ግዛት ሆናለች።
የሕዝብ እንደራሴዎች ሕጉን ሲያጸድቁ በርካቶች ሀሴታቸውን ገልጸዋል። ሕጉ ሲጸድቅ በደስታ የተቃቀፉ የሕዝብ ተወካዮችም ነበሩ።
በአውስትራሊያ ቪክቶሪያ በተባለችው ግዛት ከሁለት ዓመት በፊት የፍቃድ ሞት ሕጋዊ ሲደረግ፤ በግንባር ቀደምነት ለመሞት የወሰኑት ጽኑ የካንሰር ህመም ያለባቸው ሴቶች ነበሩ።
አወዛጋቢው ሕግ በፐርት ግዛት ከመጽደቁ በፊት ለሳምንታት የጦፈ ክርክር ተደርጎበታል። የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ሮጀር ኩክ ዜናውን ሲሰሙ የደስታ እንባ ተናንቋቸው ነበር።
አንዳንዶች አደገኛ ሲሉ የፈረጁት ይህ ሕግ 100 ቅድመ ሁኔታዎች አሉት።
በፈቃዱ ለመሞት የወሰነ ሰው በሕጉ ከለላ ከማግኘቱ በፊት በጠና እንደታመመና ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሕይወቱ ሊያልፍ እንደሚችል ማስረጃ ማቅረብ አለበት። የሁለት ገለልተኛ ሀኪሞች ፊርማም ያስፈልጋል።
የህክምና ተቋሞች ሕጉን ለማስተግበር እስኪዘጋጁ 18 ወር የተሰጣቸው ሲሆን፤ ከዛ በኋላ ሕጉ በተግባር ይውላል።












