ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከፍየል ለምድ በሚሠራ ክር ሳቢያ የተቧቀሱት የሌሴቶ እንደራሴዎች
የሌሴቶ ፓርላማ ውስጥ የሕዝብ እንደራሴዎች መደባደባቸው፣ ሰነዶችና ሌላም ቁሳ ቁስ እርስ በእርስ መወራወራቸውም ተሰምቷል።
ግብግቡ የተነሳው ከፍየል ለምድ የሚሠራ ክር (ሞሂር) ንግድ ሕግን በተመለከተ ነው።
ሞሂር በመባል የሚታወቀው ክር የሚሠራው ከፍየል ለምድ ሲሆን፤ ለስላሳ ስለሆነና ቅንጡ ምርት መሆኑ ስለሚታመን ውድ ነው። እንዲያውም አንዳንዶች 'እንቁ ክር' ይሉታል። ሞሂር የሌሴቶ ቀዳሚ ምርት፤ የብዙ ነዋሪዎቿ ቋሚ የገቢ ምንጭም ነው።
በያዝነው ዓመት መባቻ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2018 ላይ የተላለፈ ድንጋጌን ተቃውመው ፓርላማ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ነበር። ድንጋጌው አርሶ አደሮቹ የሞሂር ምርታቸውን ለቻይናዊ ደላላ (ጉዎሂ ሺ የተባለው ግለሰብ ለከፈተው ሌሴቶ ውል ሴንተር የተባለ ድርጅት) እንዲሸጡ የሚያስገድድ ነበር።
አርሶ አደሮቹ እንዳሉት፤ ደላላው ለምርታቸው እየከፈለ አልነበረም። ይህን ተከትⶀ የተነሳው ቀውስ ወደ 48,000 አርሶ አደሮች ከአንድ ዓመት በላይ ገቢ እንዲያጡ ማድረጉን የደቡብ አፍሪካው ቢዝነስ ላይቭ መጽሔት ዘግቧል።
በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ከተካሄዱ በኋላ አወዛጋቢው ድንጋጌ በጠቅላይ ሚንስትር ቶም ታባኔ ተሽሮ ነበር። ሆኖም ግን አርሶ አደሮቹ ደስተኛ አልሆኑም።
ለቻይናዊ ደላላ የመሸጥ ግዴታ የጣለው ሕግ ቢሻርም፤ ሞሂር ለጨረታ የሚቀርበው ከሌሴቶ ሳይሆን ከአጎራባቿ ደቡብ አፍሪካ እንዲሆን መወሰኑ ሌላ ችግር ፈጥሯል። የሌሴቶ አርሶ አደሮችም ፍትሀዊ ገበያ ባለማግኘታቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ጥቅምት ላይ ይህ ሕግ ተሽሮ በሌላ እንዲተካ ቢወሰንም፤ የአዲሱ ድንጋጌ ረቂቅ አልተጠናቀቀም።
የሌሴቶ አርሶ አደሮች እና ተቃዋሚዎች፤ ምርታቸውን ከአገራቸው ብቻ ከሸጡ፤ ገዢዎች የመጓጓዣ ወጪ ለመቀነስ ሲሉ ወደሌላ አካባቢ ይዘዋወራሉ የሚል ስጋት አላቸው።
ፓርላማ ውስጥ የአነስተኛ ንግድ ክፍል ተቃውሞ እንደማያሰማ ያወቁት ተቀናቃኞች በነገሩ ተቆጥተዋል፤ የፓርላማው አፈ ጉባኤም ውይይቱ እንዲቆም አድርገዋል።
አንጎራ በመባል የሚታወቀው የፍየል አይነት፤ ከ12 እስከ 15 ኢንች የሚደርስ ለምድ ስለሚያበቅል በአመት ሁለቴ ይሸለታል። ሌሴቶ ከአንጎራ ፍየል በሚገኘው ሞሂር ምርት ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ይዛለች።
ደቡብ አፍሪካ ከዓለም 53 በመቶ የሚሆነውን ሞሂር ታመርታለች።
75 በመቶ የሚሆነው የሌሴቶ ነዋሪ የሚኖረው በገጠር ሲሆን፤ አብዛኛው ቤተሰብ የሚተዳደረው በሞሂር ምርት ነው። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2018 ዘርፉ መቶ ሚሊዮን ዶላር ተገምቶ ነበር።