ዘመድ አዝማድ ፊት የሚነሳቸው ከስደት ተመላሾች

«በስደት አውሮጳ መግባት ቢያቅተን - ቤሰተቦቻችን ከዱን»

በርካታ ምዕራብ አፍሪቃዊ ስደተኞች አገራትን አቆራርጠው አውሮፓ መግባት ሲያቅታቸው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ። እልል ብሎ የሚቀበላቸው ግን ብዙ አይደለም። ኧረ እንደውም መገለል የሚደርስባቸው አሉ።

ሴራሊዮን ውስጥ ከስደት ተመላሾች ከቤተሰብ እና ዘመድ አዝማድ መገለል ይደርስባቸዋል። የውድቀት ምሳሌ ተደርገው ነው የሚቆጠሩት። ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ሰርቀው መንገድ ጀምረው የተመለሱም የትየለሌ ናቸው።

አስከፊ ታሪኮች

ፋጥማታ ለስድስት ወራት እንደባርያ ያሳለፈችውን ጊዜ ስታስብ እንባ ይቀድማታል። ሰሃራ በረሃ ላይ ያገኛት አንድ የቱዋሬግ ጎሳ አባል 'ንበረቱ' አደረጋት።

«አሕመድ ይሉታል። በጣም ግዙፍ እና ክፉ ነበር። ጥቁር ነሽ፤ ባሪያዬ ነሽ ይለኛል። ጥቁሮች ከሲዖል የመጣችሁ ናችሁ ይለኛል፤ በየቀኑ ያሰቃዩኝ ነበር።»

ለ28 ዓመቷ ፋጥማታ ይህ መጀመሪያው እንጂ የስደት ታሪኳ መቋጫ አልነበረም። ከሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ስትወጣ ምዕራብ አፍሪካን ተሻግራ በሜዲትራኒያንን ባሕር በኩል አውሮፓ ለመድረስ ነበር።

ከአሕመድ ያመለጠችው ፋጥማታ አልጄሪያዊያን ሰው አዘዋዋሪዎች እጅ ላይ ወደቀች። እዚህም እንዲሁ ስቃይና እንግልት የየዕለት ፈንታዋ ሆነ። ከአልጄሪያዊኑ ያመለጠችው ፋጥማታ ከዚህ ላይ ስቃይ መሸከም አልቻለችም። ይሄኔ ነው ወደ አገሯ ለመመለስ የቆረጥችውና ለዓለም አቀፉ የስደተኞች መሥሪያ ቤት [አይኦኤም] ያመለከተችው።

ከሁለት ዓመታት የስደት ጉዞ በኋላ ፋጥማታ ባለፈው ታህሳስ ፍሪታውን ገባች። በናፍቆት አቅፎ የተቀበላት ግን አልነበረም። አሁን ስምንት ዓመት የሆናት ልጇንም ሆነ እናቷን ካየች 2 ዓመታት ቢቆጠሩም ተመልሳ መምጣቷ ቤተሰቡን አስከፋ እንጂ አላስደሰተም።

«በመመለሴ እጅግ ደስተኛ ነኝ ግን ባልተመለስኩ ኖሮ እያልኩ አስባለሁ።»

ፋጥማታ

እንደተመለሰች ስልክ የመታችለት ወንድሟ <አንቺ መመለስ ሳይሆን እዚያው መሞት ነበር የሚገባሽ> የሚል ምላሽ ነው የሰጣት። ምክንያቱ ደግሞ ምንም ይዘሽ አልመጣሽም ነው። ከዚህ በኋላ ወንድሟን የማየት ጉገቷ ከስሞ ቀረ። ቤተሰቦቿ ቢያዝኑም ፊት ሊነሷት አልሻቱም።

ፋጥማታ ለስደት ወጪ መሸፈኛ ብላ 2600 ዶላር ከቤተሰብ ሰርቃ ነው የተሰወረችው። በወቅቱ ሃገሬው ምንዛሬ 25 ሚሊዮን ሌዮንስ መሆኑ ነው። ገንዘቡን የሰጠቻት አክስቷ ናት። አክስቷ ለምታስተዳድረው ቡቲክ ልብስ መግዣ ይሆን ዘንድ።

«አውሮፓ ተሳክቶልኝ ብገባ ኖሮ ገንዘቡን ሦስት እጥፍ አድርጌ ለአክስቴ ለመመለስ እና እናቴን ለመርዳት ነበር ሃሳቤ።»

ይህ የፋጥማታ ብቻ ታሪክ አይደለም፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ አውሮፓ መሄድ አስበው ሳይካላቸው የተመለሱ ከ3ሺህ በላይ ሴራሊዮናዊያን የሚጋሩት ታሪክ እንጂ።

በፊት በፊት ቤተሰብ ራሱ ገንዘብ አዋጥቶ ነበር ልጆችን ለስደት የሚያጨው። አሁን ግን መንገድ ላይ የሚያጋጥማቸው እስርና እንግልት ሲሰማ ነገሮ ች መቀየር ጀመሩ። ስደት ያሰቡ ወጣቶች ዕቅዳቸውን ለማንም አያካፍሉም። ድንገት ከቤተሰብ ገንዘብ ይሰርቁና ቅያሪ ልብሳቸውን አንጠልጥለው በማሊ በኩል የስደት ጉዟቸውን ይጀምራሉ።

የ21 ዓመቷ ጃሚላቱ ከፋጥማታ ጋር የተገናኙት አልጄሪያ ውስጥ ካለ እስር ቤት ነው። ጃሚላቱ ከእናቷ ቦርሳ የሰረቀችውን 3500 ዶላር ይዛ ነው የተሰወረችው። ሦስት ልጆቿን ለአባታቸው ጥላ ስደትን የመረጥችው ጃሚላ ከተመለሰች ወዲህ ከእናቷ ጋር ዓይን ለዓይን አልተያየችም ነበር።

«በገንዘቡ ምክንያት እናቴ ልታናግረኝ አትፈልግም ነበር» ትላለች።

ጃሚላ እናቷን ስታገኛት ዓይኗን ቀና ብላ ማየት አልተቻላትም። ተቃቅፈው ከተሳሳሙ በኋላ እግሯ ላይ ወድቃ ይቅርታ ጠየቀቻት። ከዚያ በኋላ የእናቷን መንደር ለቃ ወደ ፍሪታውን ተመለሰች።

ፋጥማታም ሆነች ጃሚላቱ ሥራ-አጥ ናቸው። እንዴት ያለ ሥራ ሠርተው ብድራቸውን እንደሚመልሱ አያውቁም። አንድ ያላቸው ተስፋ ሕገ ወጥ ስደት ላይ የሚሠራ አንድ ድርጅት ነው። ድርጅቱ የሴራሊዮን መንግሥት ከስደት ለተመለሱ እርዳታ እንዲያደርግ የሚወተውት ነው።

ዘመድ አዝማድ ፊት የሚነሳቸው ከስደት ተመላሾች
የምስሉ መግለጫ, ዘመድ አዝማድ ፊት የሚነሳቸው ከስደት ተመላሾች

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የሆነው ከስደት ተመላሹ ሼኩ ባንጉራ ማደሪያ ላጡ ከስደት ተመላሾች ቤት ያፈላልጋል። ሥነ ልቦናዊ እርዳታ እንዲያገኙም ደፋ ቀና ይላል።

ድርጅቱ አባል የሆነው አሊማሚ ከሦስት ዓመት በፊት ሳሃራን አቋርጦ አውሮፓ ለመግባት የተነሳው የአያቱን ውሃ ማሸጊያ ማሽን ሸጦ ነው። ከጓደኞቹ አንዱ የበረሃ ሲሳይ ሆነ። ሁለተኛው ደግሞ የሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ቀረ። መጨረሻው ሊቢያ የሆነው አሊማኒ በአይኦኤም እርዳታ ከትሪፖሊ ወደ ፍሪታውን ተመለሰ።

አይኦኤም በፈቃዳቸው ወደ መጡበት ሃገር ለሚመለሱ ስደተኞች መልሶ መቋቋሚያ 1500 ዩሮ ይለግሳል፤ 48 ሺህ ብር ገደማ መሆኑ ነው። ነገር ግን ገንዘቡን በጥሬ ለተመላሾቹ አይሰጥም። ቢሆን ኖሮ ተመላሾቹ የሰረቁትን ገንዘብ መልሰው በተገላገሉ ነበር። ድርጅቱ ገንዘቡን የሚሰጠው በዓይነት ነው፤ ተመላሾቹ ሊያቋቁሙ ላሰቡት ቢዝነስ ንብረት በመግዛት።

ፋጥማታ እና ጃሚላቱ የመልሶ ማቋቋሚያው ገንዘብ አልደረሳቸውም። ምክንያቱም በማሊ በኩል በአውቶብስ ተሳፍረው በመምጣታቸው ነው። ድርጅቱ መልሶ ማቋቋሚያ እንደሚሰጥ የሰሙ ሰዎች እየተሳፈሩ ተመላሽ ነን በማለታቸው ምክንያት ድርጅቱ በአውቶብስ ለመጡ ይህን ማድረግ አይቻለኝም አለ።

ለፋጥማታ እና መሰል ተመላሾች 'ማን እንደ ሃገር. . .' የሚለው አባባል የሚሠራ አይመስልም። ብዙዎቹ የተመለሱባትን ቀን አብዝተው ይረግማሉ። ቤተሰብ ዓይናቸውን ሊያይ አይሻም። ዘመድ አዝማድ ሲያያቸው ይሸሻል። ጎረቤቱ አፉን ያጣምምባቸዋል። ብዙዎቹ ስደትን ለመደግም ስላለመሻታቸው ምንም ማረጋገጫ የለም።