ኮንጎ፡ ሦስት ዶክተሮች የሕክምና ቡድን አባላትን በመግደል ተጠርጥረው ተያዙ

ሪቻርድ ሞኡዞኮ

የፎቶው ባለመብት, WHO/Twitter

ሦስት የኮንጎ ዜግነት ያላቸው ዶክተሮች የዓለም ጤና ድርጅት የሕክምና ቡድን አባላትን በመግደል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአገሪቷ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ካሜሮናዊው ዶክተር ሪቻርድ ሞኡዞኮ በሆስፒታል ውስጥ የኢቦላ ሕመምተኛ እያከመ እያለ በተተኮሰበት ጥይት የሞተው ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ነበር።

በወቅቱ የዓለም ጤና ድርጅት "ሥራ ወዳዱ የሕክምና ባለሙያ ምን ጊዜም የእርሱን እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ወዳሉበት ለመሄድ ዝግጁ ነበር" በማለት አሞካሽቶት ነበር።

ጥቃቱ ስለተፈፀመበት ሰበብ የታወቀ ነገር የለም።

ዶ/ር ሞኡዞኮ በዓለም ጤና ድርጅት በኮንጎ ያለውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመግታት ከተመደቡ የሕክምና ባለሙያዎች አንዱ ነበር።

አብረውት የሰሩ የማዳጋስካር፣ ካሜሮንና የኮንጎ ዜግነት ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎች በሥራው ታታሪ እንደነበረና በመቶዎች የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎችንና ዶክተሮችን ማሰልጠኑን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ 1ሺህ 800 ሰዎች በኢቦላ ተይዘው የሞቱ ሲሆን የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት የታጠቁ አማፂያንና የውጪ የሕክምና ድጋፍ ላይ ያለው ጥርጣሬ እያደናቀፈው ይገኛል።

ከፍተኛ የመከላከያ ኃይሉ አቃቤ ሕግ የሆኑት ሌተናል ኮሎኔል ዤን ባፕቲስቴ ኩምቡ፣ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የታጠቁ አማፂያን የቡቴምቦ ሆስፒታልን ጨምሮ የሕክምና ተቋማትን በማጥቃቱ ውስጥ የተሳተፉት ላይ እየተደረገ ባለው ምርመራ አራት ዶክተሮች ከጥቃቱ ጀርባ መሆናቸው ተደርሶበታል ብለዋል።

ሦስቱ ኮንጓዊ ዶክተሮች በ"ሽብር" እና "ወንጀልን በማቀነባበር" ይከሰሳሉ መባሉን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘግቧል። አራተኛው ዶክተር ግን ገና በቁጥጥር ሥር አለመዋሉንና በፍለጋ ላይ መሆናቸው ተገልጧል።

በአሁን ሰዓት በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የጀመረው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ሲሆን በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በሃገሪቱ ውስጥ ከተገኘበት ከአውሮፓዊያኑ 1976 ወዲህ ይህ በስፋቱ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ከዚህ በፊት በምዕራብ አፍሪካ ከአውሮፓዊያኑ 2014-16 ድረስ ተከስቶ በነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ 28ሺህ 616 ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 11ሺህ 310 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አብዛኞቹ የኢቦላ ወረርሽን ተጠቂዎች የጊኒ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን ሃገራት ዜጎች ነበሩ።