ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፡ ኢቦላን የሚያክሙ ሐኪሞች የሞት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው

የጤና ባለሙያዋ የአራት ቀናት እድሜ ያለውና በኢቦላ የተጠረጠረ ህፃን አቅፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለፈው ዓመት ብቻ 1ሺህ 800 ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ ሕይወታቸው አልፏል

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየሞከሩ ያሉ የጤና ባለሙያዎች የሞት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑ ተገለፀ።

ኢቦላን ለመዋጋት እየሰሩ ያሉት ዶ/ር ፓስካል ቫህዌሬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰዎች ፈፅሞ ኢቦላ የሚባል በሽታ እንደሌለ ያስባሉ ብለዋል።

ምንም እንኳን ኢቦላ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ቢሆንም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የታጣቂዎችንና የደቦ ጥቃትን እየተጋፈጡ ነው።

በአገሪቷ በማህበራዊ ድረ ገፆች እንደ ሰደድ እሳት በስፋት እየተዛመተ ያለው አሉቧልታ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሷል።

" የሚሰራጩት ሐሰተኛ መረጃዎች ሰዎች ኢቦላ ለፖለቲከኞች ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ እንደሆነ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል" ይላሉ ዶ/ር ቫህዌሬ።

እርሳቸው እንደሚሉት አንዳንዶች ሕክምናው ሰዎችን ለመግደል ታስቦ የሚሰጥ እንደሆነ ያምናሉ።

በዚህም ምክንያት በዚህ ዓመት ብቻ በትንሹ ሰባት የጤና ባለሙያዎች ተገድለዋል።

ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ 198 በሚሆኑ የሕክምና መስጫ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል። በጥቃቱም 7 ሰዎች እንደሞቱና ሌሎች 58ቱ ላይ ጉዳት እንዳጋጠመ የዓለም የጤና ድርጅት የኮሚዩኑኬሽን ኃላፊ ሳኩያ ኦካ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህም የኢቦላ ሥርጭትን በቶሎ ለመግታት አዳጋች አድርጎታል ተብሏል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱ የተረጋገጠው ባለፈው ዓመት ነበር።

የአለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በእነዚህ ጊዜያት 2577 የኢቦላ ታማሚዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል። ከእነዚህ መካከልም ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት (1790) በወረርሽኙ ሕይወታቸው አልፏል።

የሟቾቹ ቁጥር እየጨመረ እንደመጣ የተነገረ ሲሆን በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ብቻ 254 ሰዎች ሞተዋል።

ዓለም አቀፍ የጤና ቡድንም ከአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተቻለው እያደረገ ቢሆንም ለራሳቸው ሕይወት ግን ስጋት ገብቷቸዋል።

እስካሁን በኢቦላ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 170 ሺህ ያህል ሰዎች ክትባት መሰጠቱም ተገልጿል።