በአዲስ አበባ አዲስ የቤቶች ልማት ፕሮግራም ሊጀመር ነው

የአዲስ አበባ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤ አዲስ የቤቶች ልማት ፕሮግራም እንደሚጀምር አስታወቀ።

ምክር ቤቱ የ2011 አፈፃፀም ሪፖርት በዛሬው ዕለት ሐምሌ 25፣ 2011ዓ.ም ያቀረበ ሲሆን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ችግር ለመቅረፍ አዲስ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

"ለዚህም 1500 ሄክታር መሬት ይዘጋጃል፤ የግሉ ዘርፍም ይሳተፍበታል" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የከተማ አስተዳደሩ ካከናወናቸው ስራዎችም መካከል ከተማ ውስጥ ረዥም ዓመታት ለልማት ተወስደው ሳይለሙ የቀሩ 25 ሺህ ቦታዎች በአጠቃላይ 600 ሄክታር የሚሆኑ ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በ2011 በተካሄደው የመኖሪያ ቤቶች ቆጠራ በሕገወጥ የተያዙት 3ሺህ የቀበሌ ቤቶች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦችና አረጋውያን እንዲከፋፈል መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ባለፈው ዓመት 163ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው በ2012 ደግሞ ለ250ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ችግር ሆኖ ያለውን ሕገወጥ ንግድ በመቀነስ ረገድ 13 ሺህ የሚሆኑ ሕገወጥ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ አሰራር እንዲገቡ መደረጉን ጨምረው ገልፀዋል።

አስተዳደሩ በ2011 አከናወንኳቸው የሚላቸው በጎ ተግባራት

ምክትል ከንቲባው አክለውም የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችን ወደተሻለ ሕይወት ለመመለስ ጥሪ እያደረጉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን በዚህ ዓመት ጎዳና ላይ የነበሩ 10 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችና ሕፃናት ከመንገድ ላይ በማንሳት የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ የተቀሩት ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል ብለዋል።

በ2011 ዓ.ም የስራ ዘመን በመቶ ሚሊዮን ብር የሚገመት የበጎ አድራጎት ሥራ እንደተሰራ የተናገሩት አቶ ታከለ በከተማ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና የአረጋውያን ቤቶች እንዲታደስ መደረጉን ተናግረዋል

ይህ የበጎ አድራጎት ስራም በከተማዋ ሕብረተሰብ ባህል እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።

ከተማዋን እየተፈታተኗት ያሉ ጉዳዮች

በሌላ በኩል ሕገወጥ የገንዘብ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ነዳጅን አከማችቶ በማቆየት በድብቅ መሸጥ፣ በሞተር ብስክሌት የታገዘ ዘረፋ፣ ትልቅ የከተማዋ ደህንንት ስጋት ሆነው መቆየታቸውን ገልጠዋል።

ሕግን በማስከበር በኩል በተሰራው ስራም በተለይ በሞተር ብስክሌቶች እንዲታገዱ በማድረግ ዝርፊያ በከተማ ውስጥ እንዲቀንስ መደረጉን አብራርተዋል።

"ከ200ሺህ ነዋሪዎች ጋር ተገናኝተን ተወያይተናል"

በከተማዋ ውስጥ ያሉት የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጠው በዚህ መሰረት "ባለፈው ዓመት ሁለት መቶ ሺህ የሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በቀጥታ ተገናኝተን ተወያይተናል" ያሉት ምክትል ከንቲባው በተጨማሪም በመንግስት ድርጅቶች ውስጥ የሚታዩትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመቅረፍም አዋጆችና መመሪያዎች ለማሻሻል መሰራቱን ተነግሯል።

ከዚህ ውጪም ቀልጣፋ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ እንዲደርስ ለማድረግ መቶ ሺህ ለሚሆኑ ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

የምክር ቤቱ ጉባዔ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የ2012 የሥራ ዘመን ረቂቅ እቅድ በማፅደቅ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።