ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ፡ ስደተኞችን ወደ እንግሊዝ እንዲያቋርጡ የረዳው ኢማም ዘብጥያ ወረደ
የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ስደተኞች በአየር በተሞላ ጀልባ ወደ እንግሊዝ እንዲያቋርጡ ረድቷል ያለውን ኢማም በሁለት አመት እስር ቀጣ።
የ39 አመቱ ኢራናዊ በርካታ ስደተኞች ከሰሜናዊ ፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ እንዲያቋርጡ አመቻችቷል በሚል ክስ ቀርቦበት ነበር።
ኢማሙ በሚሰብክበት መስጂድ የሚካፈል የ29 አመቱ ሴኔጋላዊ በምስክርነት ቀርቧል።
ኢማሙ ዘጠኝ ወር ዘብጥያ ወርዶ ካሳለፈ በኋላ ለሶስት አመት ደግሞ ኖርድ እና ፓስ ዴ ካሊስን እንዳይጎበኝ እግድ ተጥሎበታል።
በፈረንሳይ መገናኛ ብዙኀን ማንነቱ ያልተገለፀው ኢማም የፍርድ ውሳኔውን ሲሰማ ራሱን ስቶ ወድቋል።
ኢማሙ ስድስት ወይም ሰባት በአየር የሚሞሉ ጀልባዎችን መስጠቱን ማመኑ ተዘግቧል።
ምርመራው የተጀመረው ባለፈው መጋቢት ወር በሰሜናዊ ፈረንሳይ ባህር ዳርቻ የሕይወት አድን ጃኬት፣ ጀልባና መቅዘፊያ ከተገኘ በኋላ ነው።
እንደ አቃቤ ሕግ መረጃ ከሆነ ኢማሙ ከተደራጁ የሕገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን ለሚያቀርበው እያንዳንዱ ጀልባም ኮሚሽን ይቀበል ነበር ተብሏል።
ፖሊስ ሁለት ጀልባዎችን እና ተያያዥ ቁሳቁሶችን በኢማሙ መኖሪያ ያገኘ ሲሆን ሁለት ሰዎች ከእርሱ ጀልባ መግዛታቸውን የእምነት ቃላቸውን ሰትተዋል ተብሏል።
ኢማሙም በቤልጂየም ድንበር የሚገኝ አንድ ሱቅ በመሄድ ጀልባውን መግዛቱን ተናግሯል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ በአነስተኛ ጀልባ የሚያቋርጡ ስደተኞች እየተበራከቱ መጥተዋል።