ዋትስአፕን በመጠቀም የስለላ መተግበሪያ ተጭኖ ነበር ተባለ

ዋትስአፕን በመጠቀም የስለላ መተግበሪያ ተጭኖ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች (ሀከርስ) የዋትስአፕ መተግበሪያን ተጠቅመው ስልኮችና ሌሎችም የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ላይ መሰለያ ጭነው እንደነበረ ተረጋገጠ።

መሰለያውን የጫኑት የዋትስአፕ መተግበሪያ ላይ ያለ ክፍተትን ተጠቅመው ነው ተብሏል።

በፌስቡክ ስር የሚተዳደረው ዋትስአፕ ይፋ እንዳደረገው፤ ጥቃቱ የተመረጡ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን ኢላማ ያደረገ ነበረ። የተቀነባበረውም የላቀ ችሎታ ባላቸው ሀከሮች ነው ተብሏል።

ፋይናንሽያል ታይምስ እንደዘገበው፤ ጥቃቱ የተሰነዘረው 'ኤንኤስኦ' በተባለ የእስራኤል የደህንንት ተቋም ነው።

ባለፈው ሀሙስ ዋትስአፕ የተፈጠረውን ችግር ማስተካከል ችያለሁ ብሏል።

ጥቃቱ እንደተሰነዘረ የታወቀው በያዝነው ወር መባቻ ላይ ሲሆን፤ ሰኞ እለት ዋትስአፕ 1.5 ቢሊየን ተጠቃሚዎቹ የተሻሻለውን መተግበሪያ እንዲጭኑ (አፕዴት እንዲያደርጉ) ጠይቆ ነበር።

መሰለያ የጫኑት አካሎች በዋትስአፕ መሰለል ወደሚፈልጉት ግለሰብ ይደውላሉ። ከዛም መሰለያውን ይጭናሉ። ግለሰቡ ስልኩን ባያነሳም እንኳን መሰለያውን ከመጫን አያግዳቸውም ተብሏል።

ፋይናንሽያል ታይምስ እንዳለው ከሆነ ጥሪ ያደረገው አካል ማንነት ከደዋዮች ዝርዝር (ኮል ሎግ) ይጠፋል።

ዋትስአፕ ለቢቢሲ እንዳሳወቀው፤ ለመጀመርያ ጊዜ ይህ ክፍተት መፈጠሩን ያስተዋለው የድርጅቱ የደህንነት ክፍል ነበር።

ወዲያው ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እንዲሁም ለአሜሪካ 'ዲፓርትመንት ኦፍ ጀስቲስ' አሳውቀዋል።

"ጥቃቱ ከግል ድርጅት መሰንዘሩን የሚያሳይ ምልከት አለ። ከመንግሥት ጋር በመሆን ያልተፈለገ የስለላ ሶፍትዌር (ስፓይዌር) በመጠቀም ስልክ መቆጣጠር የሚያስችል ነው" ሲሉ ለመገናኛ ብዙኀን ገልጸዋል።

'ኤንኤስኦ' ከመንግሥት ፍቃድ የተሰጣቸው ተቋሞች ወንጀልን ለመከታከልና የሽብር ጥቃት እንዳይደርስ ለማድረግ እንዲያውሉት አልሞ የሠራው ነው። ሆኖም አሠራሩ ያላግባብ ጥቅም ላይ ውሎ ከሆነ ምርመራ ይደረጋል ተብሏል።

ዋትስአፕ ምን ያህል ሰዎች ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ለማወቅ ጊዜው ገና ነው ብሏል።

ከዚህ ቀደም በኤንኤስኦ ጥቃት ደርሶብኝ ነበር ያለው የመብት ተከራካሪው አምንስቲ ኢንተርናሽናል፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መሰል ጥቃት ሊደረስባቸው እንደሚችል ስጋት ነበረን ብሏል።

የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የቴክኖሎጂ ክፍል ዳይሬክተር ዳና ሌግሌቶን እንዳሉት፤ ታዋቂ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞችን ለመቆጣጠር በመንግሥታት ጥቅም ላይ የሚውል አሠራር ነው።

የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር የ'ኤንኤስኦ'ን ፍቃድ እንዲቀማ ለመጠየቅ በአምንስቲ ኢንተተርናሽናል የተመራ የፊርማ ስብስብ ቴል አቪቭ ፍርድ ቤት ይቀርባል።