በአፋር ክልል በተፈጸመ ጥቃት የሰው ህይወት መጥፋቱ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
መጋቢት ሰኞ 16 እና መጋቢት ማክሰኞ 17 በአፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ ከጎረቤት ሀገራት መጡ የተባሉ ታጣቂዎች ጥቃት አደረሱ። ጥቃቱ የተፈፀመው ከሶማሌ ላንድ እና ከጅቡቲ አዋሳኝ አካባቢዎች በኩል በገቡ ኃይሎች መሆኑን የክልሉ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ኻሌይታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሎጊያ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብዱ አሊ መሀመድ ይህ ጥቃት ከአሳይታ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ አዋሳኝ ቀበሌ ላይ እንደተፈፀመ አረጋግጠዋል። አክለውም ጥቃት አድራሾች በተለያየ ጊዜ ገዳማይቱና እንዱፎ በሚባል አካባቢ ገብተው እንደነበር ያስረደሉ።
በአካባቢው መከላከያ መኖሩን የሚያስታውሱት አቶ አብዱ ከሁለት ወር በፊት እንዱፎ ላይ የአፋር ባንዲራን አውርደው ማቃጠላቸውን እና በአካባቢው በነበረ የፀጥታ ኃይል ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህ በኋላም በተለያዩ የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈፀም ተናግረው፤ በአካባቢው በገዳማይቱ እስከ ሀርጌሳ የሚያገናኝ የኮንትሮባንድ መንገድ መኖሩን አንስተው ገዳማይቱ በኮንትሮባንድ ንግድ እንደ ቶጎጫሌ እጅግ በጣም ታዋቂ መሆኗን ይናገራሉ።
ይህ የኮንትሮባንድ ንግድ በአደባባይ የሚካሄድ ሲሆን ውስጥ ለውስጥ የሚያገናኙ የኮንትሮባንድ መንገዶች መኖራቸው የአካባቢውን አርብቶ አደር ለጥቃት ማጋለጡን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
እነዚህ ጥቃት አድራሾች መጋቢት 16 ሰኞ እለት ጀምረው በስፍራው እንደቆዩ መስማታቸውን አስታውሰው ድንገት ግመል የሚፈልጉ ሰዎች ወደ ስፍራው ሲሄዱ ጥቃት መክፈታቸውንና አንድ ሰው መሞቱን እንዲሁም አንድ ሰው ደግሞ መቁሰሉን አረጋግጠዋል።
ከዚያ በኋላ በታጣቂዎቹና በአርብቶ አደሮቹ መካከል የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉን በነጋታው ማክሰኞም ታጣቂዎቹ ስፍራውን ለቀው መሸሻቸውን ያስረዳሉ።
የክልሉ የፀጥታና የደህንነት ቢሮ ኃላፊው አቶ አህመድ ሱልጣን የደረሰውን ጥቃትና የጠፋውን የሰው ህይወት አረጋግጠው የተፈጠረውን ሁኔታ ሲያስረዱ፤ በዱብቲ ወረዳ ገዊሊ በሚባል ስፍራ በወቅቱ ፍየል ለመጠበቅ ከአካባቢያቸው ወጣ ብለው የነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩንና በኋላም የአካባቢው ማህበረሰብ ጥቃቱን ለመከላከል ተኩስ መክፈቱን ታጠቂዎቹም መኪናቸውን ይዘው መሸሻቸውን አስረድተዋል።
ግጭቱ የተከሰተው በዱብቲና አሳይታ ወረዳ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው አራት የታጠቂዎቹ ተሽከርካሪዎች ማምለጣቸውን ነገር ግን አንድ የጭነት መኪና መያዙን አስረድተዋል።
በአካባቢው የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች የሚጠቀሙበት ከጅቡቲ እንደፎ፣ ገደማይቱና አዳይቱ የሚወስድ መንገድ መኖሩን ያረጋገጡት ኃላፊው በአካባቢው ይህ ጥቃት ሲደርስ መንገድና የስልክ ኔትወርክ ባለመኖሩ ዘግይተው መስማታቸውን ያስረዳሉ።
በአካባቢው የጦር መሳሪያን ጨምሮ ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድ አንደሚካሄድ መረጃው እንዳላቸውም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እነዚህ ቡድኖች የአፋር አርብቶ አደሮች ላይ ተዘጋጅተው ጥቃት ለማድረስ የመጡ ይመስላል የሚሉት አቶ አህመድ፤ ጥቃት አድራሾቹ የሚመገቡትን ሩዝና ስኳር፣ የሚጠጡትን ውሃ እንዲሁም ሲሚንቶና ቆርቆሮ ይዘው መምጣታቸውን ገልፀዋል።
አክለውም ጥቃት ፈጻሚዎቹ ጥይት ይዘውባቸው የነበሩ ካርቶኖች በስፍራው መያዛቸውንም አረጋግጠዋል።
"ታጣቂዎቹ ካምፕ ለመመስረት የመጡ ይመስላሉ" ያሉት የክልሉ የፀጥታና የደህንነት ቢሮ ኃላፊ፤ አሁን በቁጥጥር ስር የዋለው መኪና ሁለት ሰሌዳዎችን መጠቀሙን ያስረዳሉ። ከፊት የለጠፈው ሦስት ቁጥር ኢቲ የሀገራችን ሲሆን በጀርባ በኩል ደግሞ የሶማሌ ላንድ ሰሌዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የክልሉ ኮሙኑኬሽንም ሆነ የፀጥታ እና ደህንነት ኃላፊዎች እንደሚናገሩት ጥቃቱ በተደራጁ ቡድኖች የተፈመ መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች የተገኙ መረጃዎች አሉ። የአልሸባብ ባንዲራ፣ የፊት መሸፈኛ ጭምብል፣ የሶማሌ ላንድ ሰሌዳ ቁጥር እና የ ጅቡቲ መታወቂያ በማለት ያብራራሉ።
የደህንነትና የፀጥታ ኃላፊው አክለውም ከዚህ ጥቃት ጋር ተያይዞ በአሳይታ ከተማ ይኖር የነበረ አንድ የጅቡቲ ዜግነት ያለው ሰው በቁጥጥር ስር መዋሉንም ተናግረዋል።
ይህ በድንበር አካባቢ ባሉ የአርብቶ አደሮች መካከል የሚደረግ የተለመደ ግጭት ላለመሆኑ መረጃ እንዳላቸው የተጠየቁት የክልሉ የደህንነት ኃላፊ፤ አካባቢው ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥቃቶች ማስተናገዱን አስታውሰው በፊት አርብቶ አደሮች በግጦሽና በውሃ ፍለጋ ቢጋጩም በመኪና መጥተው ስንቅ አደራጅተው እንዳልሆነ በማስታወስ "አሁኑ ግን የአልሸባብ ባንዲራ መገኘቱ፣ የሚጠቀሙት መሳሪያ እና የሚፈጽሙት ጥቃት ግጭቱ በአርብቶ አደር መካከል የሚደረግ እንዳልሆነ ያሳያል" ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።












